ቅ. ሥላሴ ካቴድራል

{gallery}pic-cathedral{/gallery}

ቅ. ሥላሴ ካቴድራል

{gallery}pic-cathedral{/gallery}

ቅ. ሥላሴ ካቴድራል

{gallery}pic-cathedral{/gallery}

ቅ. ሥላሴ ካቴድራል

{gallery}pic-cathedral{/gallery}

http://www.trinity.eotc-churches.org/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/46016501.jpg http://www.trinity.eotc-churches.org/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/7472451.jpg http://www.trinity.eotc-churches.org/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/395795church_4.jpg http://www.trinity.eotc-churches.org/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/357816church_5.jpg
የ2006 ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓል በድምቀት ተከበረ

2006

የመስቀል ደመራ በዓል ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያሪክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘ ኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘ አክሱም ወጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ብፁአን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፤የአዲስ አበባ መስተዳድር ከንቲባ ተወካይ፤ የተለያዩ ሀገራት ከፍተኛ ዲፕሎማቶችና አንባሳደሮች፣ የአዲስ አበባ ከተማ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ጥንግ ድርብ የለበሱ ሊቃውንት፣ ካህናትና ምእመናን በተገኙበት በደማቅ ስነ-ስርአት ተከብርዋል፡፡

በዓሉ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትሪያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጰሳት ዘኢትዮጵያ፣ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም፣ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ፀሎተ ቡራኬ የተጀመረው የተጀመረ ሲሆን ኢትዮጵያውያን ተቀብሮ የነበረውን እና በንግስት እሌኒ የተገኘውን መስቀል ለማሰብ በዓሉን እንደሚያከብሩት ፤ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያሪክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ተናግረዋል።

ቅዱስነታቸው ኢትዮጵያውያን የተገኘውን መስቀል በማሰብ የመስቀሉን በረከት ለማግኘት እንደሚያከብሩትም ነው የተናገሩት። የመስቀል በዓል ለዘመናት ኢትዮጵያውያን በጋራ ሲያከብሩት የቆዩት በዓል መሆኑን ያወሱት ቅዱስነታቸው ፤ ህዝቦች ተከባብረውና ተቻችለው ለመኖራቸው ተምሳሌት መሆኑንም አስረድተዋል። በመሆኑም የመስቀል በዓል በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ የሚደረገው ጥረትም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። የአዲስ አበባ ከንቲባ የአቶ ድሪባ ኩማ ተወካይ በመክፈቻ ንግግራቸው የመስቀል ደመራ በአል የሀገራችን ብሄር ብሀሄረሰቦችና ህዝቦች ለዘመናት በድምቀት ሲያከብሩት የኖሩት ሃይማኖታዊ በአል ብቻ ሳይሆን ታሪካችንን፣ የቱሪዝም ሀብቶችንና ሌሎች እሴቶቻችን ለሌላው ዓለም የምናስተዋውቅበት የማንነታችን መገለጫ ጭምር ነው ብለዋል፡፡

በበአሉ ጥንግ ድርብ የለበሱ ካህናቶችና የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች የተለያዩ ዝማሬዎችን አቅርበዋል። የደመራ መለኮስ ስነ ስርአቱ ተካሂዶ የደመራው በአል ፍጻሜ ሆኗል ፡፡

ለተጨማሪ ንባብ እዚህ ላይ ይጫኑ (‹‹የብፁዕ ወቅደስ አቡነ ማትያስ ቀዲማዊ ፓትርያርክ መልእክት››)

 
በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ለሚጦሩ አረጋወያን ለ12ኛ ጊዜ እረዳታ ተሰጠ

በመ/ር ዘሩ ብርሃኔ (Bsc)

“ለችግረኛና ለምስኪን የሚያስብ ምስጉን ነው እግዚአብሔር ከክፉ ያድነዋል፡፡” መዝ. 40÷1

“እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ”2ኛ ቆሮ. 9÷7

0002

ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ በድህረ ገፃችን አማካኝነት ወጣት ብሩክ አስራት የክርስትና ስሙ ግርማ ጽዮን ከዛሬ 12 ወራት በፊት ጀምሮ ለካቴድራሉ አረጋውያን የሚሆን በየወሩ ለአረጋውያኑ የሚያስፈልጋቸውን የምግብ እርዳታ እያደረገላቸው መሆኑን ስንዘግብ መቆየታችን የሚታወስ ሲሆን አሁንም እንደተለመደው ለ12ኛ ጊዜ ለ1 ወር የሚሆን በእነ ወ/ሮ ማርታ ወርቄ፤በወንድሙ እና በጓደኞቹ አማካኝነት እርዳታውን ልኳል፡፡

በዚሁ ዕለት በቄሰ ገበዝ አባ ገ/ዮሐንስ ወ/ሳሙኤል አማካኝነት ለወጣት ብሩክ አስራት፤ለቤተሰዎቹና ለጓደኞቹ ጸሎትና ምስጋና እንዲሁም ቃለ ምእዳን የተሰጠ ሲሆን በወጣት ብሩክ አስራት እየተደረገ ላለው ነገር ሁሉ ምስጋናቸው እጅግ የላቀ መሆኑን ገልፀው ሌሎችም የዚሁ የተቀደሰ ዓላማ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡ በመጨረሻም መልአከ ሰላም ማሩ ለወጣት ብሩክ አስራትና ለቤተ ሰዎቹ እያደረገው ላለው ነገር ሁሉ በዓጋዕዝተ ዓለም ሥላሴ ስም ካቴድራሉን በመወከል ምስጋናቸውን አቅርበዋል ፡፡

እነዚህ አረጋውያን ከዛሬ 45 ዓመታት በፊት ከዐፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስት ጀምሮ በንጉሱ አማካኝነት በካቴድራሉ በጎ አድራጎት /ምግባረ ሠናይ ክፍል ሥር በቃለ ዓዋዲ መሠረት የተቋቋመ ሲሆን ቀደም ሲል በብዙ መልኩ የተደራጀ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን አሁንም በካቴድራሉ አስተዳደር አማካኝነት እንደቀድሞ ሁሉ ለማጠናከር ከፍተኛ የሆነ ጥረት እየተደረገ ነው ፡፡

በመሆኑም በዘላቂነተ የአረጋውያኑ ችግር በመጠኑ ለመቅረፍ እንደ ወጣት ብሩክ አስራት የክርስትና ስሙ ግርማ ጽዮን አቅማችሁ የፈቀደውን/የቻላችሁትን ያህል እርዳታ እንድታድርጉ እናሳስባለን፡፡

አረጋውያኑ ከሚያስፈልጓቸው መሠረታዊ ነገሮች መካከል፡- 1. ምግብ፣ 2. መጠለያ፣ 3. ልብስና 4. ሞግዚት ናቸው፡፡ ወጣት ብሩክ አስራት ለእነዚህ አረጋውያን በየወሩ ለጤፍ 980 ብር ፣ ለዘይት 500 ብር ፣ ለበርበሬ እና ሽሮ 680 ብር፣ ለጋዝ 150 ብር፣ ስኳር 140 ብር፣ ሰሙና 86 ብር እና ለሻይቅጠል 50 ብር በድምሩ 2,586 ብር በየወሩ ለአረጋውያኑ ወጪ ያደርጋል፡፡

 
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የ2006 ዓ.ም አስመልክተው መልእክት አስተላለፉ

0908

ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ዘተናገረ በእንተ ርእሰ ዓውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወስድስቱ ዓመተ ምሕረት፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

• በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣

• ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትኖሩ፣

• የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፣

• በሕመም ምክንያት በየሆስፒታሉ ያላችሁ፣ •

እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፣ የዘመናት ፈጣሪ እግዚአብሔር አምላካችን፣ እንኳን ከሁለት ሺ አምስት ዓመተ ምሕረት ዘመነ ማቴዎስ ወደ ሁለት ሺሕ ስድስት ዓመተ ምሕረት ዘመነ ማርቆስ በሰላም አደረሳችሁ!!!

“ወሠርዐ ዕድሜሁ ወዓመታቲሁ መጠነ ይነብሩ በዘየኃሥሥዎ ለእግዚአብሔር፤ እግዚአበሔር፣ እርሱን ፈልገው ያገኙት ዘንድ፣ ሰዎች የሚኖሩባቸውን የዕድሜና የዘመናት መጠን ሠራ” (የሐ.ሥራ.17÷26-27) አምላካችን እግዚአብሔር፣ ለፍጡራን ከሰጣቸው መልካም ስጦታዎች መካከል፣ የዘመን ስጦታ የመጀመሪያውን ደረጃ ይይዛል፤ ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን፣ እግዚአብሔር በጥንተ ፍጥረት፣ ፍጥረታትን ውብ አድርጎ ሲፈጥር፣ ዘመናትንና ዕለታትን ለመለየት ያስችሉ ዘንድ፣ ብርሃናትን በሰማይ ጠፈር ፈጥሮአል፤ (ዘፍ.1÷14-19) ከዚያን ጊዜ ጀምሮ፣ የሰው ልጅ፣ በብርሃን ዑደት እየታገዘ፣ ዘመናትን፣ ወቅቶችን ፣ወራትንና ዕለታትን ለይቶ በማወቁ፣ መርሐ ግብር እያወጣ፣ ለሥራው አፈጻጸም ይጠቀምባቸዋል፤ በመሆኑም፣ ዘመናት፣ ለሥራችን የሚሰጡት ግብአት፣ ከፍ ያለ ሆኖ ይታያል፤ እግዚአብሔር፣ ዘመናትን በሰዓታት፣ በቀናት፣ በወራት በወቅቶችና በዓመታት፣ ከፋፍሎ የፈጠረበት ዋና ምክንያት፣ በእነርሱ መለኪያነት፣ አቅደን፣ አልመንና ጠንክረን በመሥራት፣ ራሳችንን፣ ቤተ ሰባችንን፣ ሀገራችንንና በአጠቃላይ ዓለማችንን፣ ለኑሮ የተመቸች፣ ውብና ለም አድርገን እንድንከባከብና እንድንጠብቅ ነው፡፡ (ዘፍ.2÷15)

የዘመን ጸጋ፣ በሥጋዊ ሕይወታችን ብቻ ሳይሆን፣ በመንፈሳዊ ሕይወታችንም ከፍተኛ ትርጉም አለው፤ የእግዚአብሔር ቃል፣ ከፍ ብሎ እንደነገረን፣ ዘመናት፣ እግዚአብሔርን ፈልገን ለማግኘት የሚያስችሉን መሣሪያዎች ናቸው፤ ይህም ማለት፣ እያንዳንዱ ዓመት፣ በሰው አእምሮ ውስጥ ጥሎት የሚያልፍ፣ ተግባራዊ ትምህርትና ዕውቀት አለ፤ ከዚህ አኳያ፣ ሰው፣ በየዓመቱ ከሚቀስመው ሰፊ ግንዛቤ፣ ዕውቀቱን እያሰፋ፣ ወደ ተሻለ ማስተዋል ይሸጋገራል፤ ጤናማ ማስተዋልን ሲያገኝ፣ ፈጣሪውን ወደ መፈለግና ወደ መከተል፣ ፍጹም ሰው ወደ መሆንም ይደርሳል፤ በዚህ ምክንያት፣ ዘመን፣ ሰው፣ ፈጣሪውን እንዲያውቅ የሚያስችል፣ የማብቃት ጸጋ አለው ማለት ነው፤ (የሐ.ሥራ. 17÷26-27)

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼ ምእመናንና ምእመናት!

እግዚአብሔር እኛን ሲፈጥር ዓላማ አለው፤ ተቀዳሚ ዓላማውም፣ በተፈጥሮ የተሰጠንን ዕውቀት ተጠቅመን፣ እርሱን እንድናውቅ፣ እርሱን እንድናምን፣ እርሱን እንድናመልክና ለእርሱ እንድንታዘዝ፣ በእርሱም የዘላለም ሕይወትና ክብር እንድናገኝ ነው፤ (ሮሜ.1÷19-21፤ ዮሐ.20÷31) በምድራዊው ኑሮአችንም እንዳንቸገር፣ ልዩ ልዩ ሀብት ያላትን ምድር ፈጥሮ ሰጥቶናል፤ ይሁንና፣ ምድራችን፣ በማኅፀንዋ የተሸከመችውን ልዩ ልዩ ጥሬ ሀብት፣ መልክና ጣዕም እንዲኖረው አድርጎ ወደ ጥቅም የመለወጡ ኃላፊነት፣ ለእኛ አስረክቦአል፤ ይህም፣ እግዚአብሔር፣ እኛን የሥራው ተሳታፊዎች የማድረግ ዓላማ ያለው መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ እግዚአብሔር፣ የሥራ ሁሉ ጀማሪ ከመሆኑም ሌላ፣ ሁሌም ሲሠራ የሚኖር፣ ሥራ ወዳድ አምላክ ነው፤ (ዮሐ. 5÷17) የእኛንም አካል ለሥራ የተመቸ አድርጎ መፍጠሩ፣ የሥራው ተሳታፊዎች እንድንሆን ብሎ እንደሆነ ልናስተውል ይገባል፤ ስለለሆነም፣ እኛ፣ ታታሪ ሠራተኞች በሆን ቁጥር፣ የእግዚአብሔር ተባባሪዎች እንሆናለን፤ ከሥራ በራቅን ቁጥር ደግሞ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ላለመተባበር እየከጀልን እንደሆነ፣ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አንጸር፣ እያንዳንዱ ሰው፣ ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ፣ በኅሊናው ማቃጨል ያለበት ዓቢይ ነገር፣ በሥጋዊም ሆነ በመንፈሳዊ ኃላፊነቴ ምን ሠራሁ? ምንስ ቀረኝ? በአዲሱ ዓመትስ ምን ሠርቼ ከእግዚአብሔር ጋር ተባባሪ ልሁን የሚለውን ነው፤ ሥራ መሥራት ማለት፣ ከእግዚአብሔር ጋር መተባበር ማለት ነውና፤ እያንዳንዱ ሰው፣ ይህንን አስተሳሰብ አንግቦ፣ አዲሱን ዘመን በአዲስ መንፈስ ከተቀበለው፣ እውነትም ዘመኑን በሥራ ወደ አዲስነት ይለውጣል፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼ ምእመናንና ምእመናት፡-

ዓይነተ ብዙ በሆነ የተፈጥሮ ጸጋ የታደለችው ሀገራችን ኢትዮጵያ፣ በተፈጥሮ ጸጋ የጎደላት የሌለ ብቻ ሳይሆን፣ ከሁሉም የበለጠና የተሻለ ሀብት ያላት ሀገር ናት፤ ነገር ግን፣ በሀገራችን ከርሰ ምድርና ገጸ ምድር ተከማችቶ የሚገኘውን ሀብት፣ ጠንክረን በመሥራት ወደ ጥቅም መለወጥ እየቻልን፣ የሌላውን ትርፍራፊ ለመለቃቀም በሚል የተሳሳተ ግንዛቤ፣ መተኪያ የማናገኝላቸውን ልጆቻችን፣ በየአቅጫው እየተጎዱብን ነው፤ ወጣት ልጆቻችን፣ ለአደጋ በተጋለጠ ሁኔታ፣ በሕገ ወጥ መንገድ፣ ከውድ ሀገራቸው እየወጡ በየአካባቢው ወድቀው እየቀሩ ናቸው፤ ይህን አሳዛኝ ሁኔታ ለማስቆም፣ ሕዝቡ በርትቶ በማስተማርና በመሥራት፣ ልጆቹን ከአሰቃቂ ሕልፈተ ሕይወት ማዳን አለበት፡፡ ሃይማኖታችንና ሀገራችንን የምንወድ ኢትዮጵያውያን ሁሉ፣ በሀገራችን ሥር ሰዶ የቆየውን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር በመቅረፍ፣ በማኅበራዊ ኑሮው የተስተካከለና በኢኮኖሚው የበለጸገ ማኅበረሰብ ለመፍጠር በሚደረገው ርብርቦሽ፣ ሁላችንም ኢትዮጵያውያን በመቻቻል፣ በመከባበር፣ በመፈቃቀር፣ በስምምነትና በመመካከር መሥራት፣ ተቀዳሚ ዓላማችን ማድረግ አለብን፤ ከሁሉም በላይ፣ የተጀመሩም ሆኑ ለወደፊት የሚጀመሩ የልማት ሥራዎች፣ ፍጻሜ አግኝተው፣ ሀገራችንን በልማት የመለወጥ ሕልማችንን እውን ሊያደርግ የሚችል፣ ሰላማችን በአስተማማኝ ሁኔታ የተጠበቀ እስከሆነ ድረስ ብቻ መሆኑን፣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ፣ ለአፍታ እንኳ ሊዘነጋው አይገባም፡፡ በመሆኑም፣ ሁላችንም ኢትዮያውያንና ኢትዮጵያውያት፣ በዘር፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋ በአካባቢ ሳንለያይ የዕድገታችን ዋስትና የሆነው ሰላማችንን፣ በንቃት መጠበቅ አለብን፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼ ምእመናንና ምእመናት፡-

የሀገር ደኅንነትና ልማት ከሚረጋግጥባቸው አንዱ፣ በአካል፣ በአእምሮና በአስተሳሰብ ጭምር፣ ሙሉ ጤናማ የሆነ ማኅበረ ሰብ ሲኖረን ነው፤ ስለሆነም፣ በሀገራችን፣ በእርግዝናም ሆነ በወሊድ ጊዜ፣ የጤና ባለሙያ ተገቢ እንክብካቤና እገዛ ባለማግኘት፣ ለሞት አደጋ የሚጋለጡ እናቶችና ሕጻናት፣ በርከት ያሉ እንደሆነ ይታወቃል፤ ይህን ለመቀነስና ለመከላከል ታስቦ፣ በሀገራችን እየተካሄደ ያለውን የእናቶችና የሕጻናት የጤና እንክብካቤ፣ የተሳካ ይሆን ዘንድ ሁሉም ሕዝባችን ሊደግፈውና በመርሐ ግብሩ ተጠቃሚ ሊሆን ይገባል፤ ሕክምና ማለት ጥበብ ማለት ነው፤ ጥበብን ደግሞ አጽንተን እንድንከተላትና እንድንጠቀምባት፣ እግዚአብሔር ያዘዘን በመሆኑ፣ በባለሙያና በሕክምና ጥበብ እየተረዱ፣ በጤና ተቅዋም መውለድ እግዚአብሔር የፈቀደውና የሚወደው ነው፤ በተለይም፣ እናቶቻችን፣ የጉዳዩን አሳሳቢነት ተገንዝበው፣ በየአካባቢያቸው በሚገኙ የጤና ተቅዋማት እየተገኙ፣ በጤና ባለሙያ ድጋፍና ርዳታ በመውለድ፣ ጤንነታቸውን መጠበቅ ይኖርባቸዋል፡፡

በመጨረሻም፣ በአዲሱ ዓመት፣ ሕዝባችን ሁሉ፣ በማኅበራዊና በኢኮኖሚያዊ ኑሮው የበለፀገ፣ በዕውቀትና በማስተዋል የተካነ፣ ጤንነቱና ሰላሙ የተጠበቀ ይሆን ዘንድ፣ በተሠማራበት የሥራ መስክ ጠንክሮ በመሥራት፣ ሀገሩን ያለማ ዘንድ፣ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡

እግዚአብሔር አዲሱን ዘመን ይባርክልን ይቀድስልን አሜን!

አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት

መስከረም 1 ቀን 2006 ዓ.ም

ባሕረ ሐሳቡን ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ (ባሕረ ሐሳብ የዘመን መቁጠሪያ)

 
ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሠራተኞች የቁጥጥርና የሥራ አመራር ሥልጠና ተሰጠ

00718

ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት እና በሥሩ ላሉ 7 ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች የሥራ ኃላፊዎች እና አጠቃላይ ሠራተኞች ከነሐሴ 22 -23 ቀን 2005 ዓ.ም. ለሁለት ቀናት የተዘጋጀ የአቅም ግንባታና ማሻሻያ ሥልጠና መርሐ ግብር ተሰጥቷል፡፡ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በ7 ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች ማለትም

1. አራዳ ጉለሌ ክ/ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት

2. የካ ክ/ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት

3. ቦሌ ክ/ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት

4. ኮልፌ ቀራንዮ ክ/ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት

5. ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት

6. ልደታ ቂርቆስ አዲስ ከ/ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት

7. አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በሚል በአዲስ መልክ መደራጀቱንና መዋቀሩን ተከትሉ ቀደም ሲል በሐምሌ /2005 ዓ.ም መልካም አስተዳደር ለዘላቂና ሁለንተናዊ የቤተ ክርስቲያን እድገት በሚል ርዕስ ለ5 ቀናት ያህል ለሀገረ ሰብከት ሠራተኞች፣ለአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና ፀሐፊዎች፣ለአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት የሰበካ ጉባኤ ምክትል ሊቃነ መናብርት፣ ለአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት የክፍል ኃላፊች፣ ለአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት የሰንበት ት/ቤት ተወካዮች ሙሉ ሥልጠና መስጠቱ ይታወቃል፡፡

እንደዚሁም ሀገረ ስብከቱ ከሐምሌ ወር 2005 ዓ.ም ጀምሮ ለ3 ወራት ያህል የሚገለግል ጊዚያዊ የሥራ አደረጃት በባለሞያዎች አዘጋጅቶና በቅዱስ ሲኖዶስ አፀድቆ ሥራ ላይ እንዲውል ያደረገ ሲሆን 2ኛው ሙሉ መዋቅርና አደረጃጀት ደግሞ ሥራውን ሙሉ ቡሙሉ በመጠናቀቅ ላይ የሚገኝ ሲሆን ከጥቅምት 30/2006 ዓ.ም ጀምሮ ሥራ ላይ ይውላል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ይህም ለሀገረ ስብከቱ በታሪከ የመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡

ይህን ተከትሎም ለ2ኛ ጊዜ ከነሐሴ 22-23/05 ዓ.ም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ተሰጥቷል በዚሁ በሥልጠና ላይ የተገኙ ባለሥልጣናትና ተሳታፊዎች 1. ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት 2. ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የወላይታ ዳውሮና ኮንታ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ 3. ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣ የሰቲት ሑመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ 4. ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትያርክ ረዳት ሊቀ ጳጳስ እና የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ 5. የሀገረ ሰብከቱ ዋና ሥራ አሥኪያጅ፣ የየክፍላተ ከተሞቹ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች ሥራ አሥኪያጆች፣ ልዩ ልዩ የሥራ ዘርፍ ኃላፊዎች እና ሠራተኞች የሥልጠናው መርሐ ግብር በቅዱስነታቸው ጸሎትና ቡራኬ ተከፍቷል፡፡ በመቀጠል ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትያርክ ረዳት ሊቀ ጳጳስ እና የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሥልጠናውን አስመልክቶ “ነገርን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው” በሚል ርዕስ የመግቢያ ንግግር አድርገዋል፡፡

ብፁዕነታቸው በመግቢያ ንግግራቸው፤ ቅዱስ ሲኖዶስ ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ይበጃል ይሆናል ያለውን ሲወስን ቆይቶ በግንቦት 2005 ዓ.ም የርክበ ካህናት ጉባዔ በወሰነው መሠረት፤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በአንድ ሀገረ ስብከት እና በሰባት ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች ተደራጅቶ ላለፉት ሦስት ወራት የአድባራት እና የገዳማት ጥያቄዎችን በፍጥነትና በተቀላጠፈ መልኩ አገልግሎት እንዲያገኝ ብርቱ ጥረት ማድረጉን በማውሳት፤ ይህን የበለጠ ለማጠናከር በሥልጠና መታገዝ አስፈላጊ መሆኑን በመረዳት በሀገረ ስብከቱና በሥሩ ለሚገኙ የክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች ይህ የአቅም ግንባታ ሥልጠና መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡ በመቀጠል ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የሥልጠናውን መጀመር በይፋ አብሥረው ባስተላለፉት ቃለ ምዕዳን እና የሥራ መመሪያ በቤተ ክርስቲያን ከላይ እስከ ታች ባለው የሥራ ኃላፊነት ላይም ሆነ በተለያየ የሥራ ዘርፍ የምንገኝ አጠቃላይ ሠራተኞች /አገልጋዮች/ ሁሉ እስከ አሁን ድረስ የቤተ ክርስቲያናችንን ስም ያስጠፋውንና መልካም ስማችንን እያጎደፈ ባለው የመልካም አስተዳደር እጦት፣ የሥነ ምግባር ጉድለት፣ ዘረኝነትና የጎጠኝነት መንፈስ ከሥር መሠረቱ ነቅለን በማስወገድ ሁላችንም ታማኞች ሆነን ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው፣ ዘመኑን የዋጀ አሠራርን መከተል እንደሚገባን ከገለጹ በኋላ የተቀመጥንበት ወንበር ትልቅ ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ በሥራችን ቸልተኛ መሆን የለብንም ብለዋል፡፡

ቅዱስነታቸው አያይዘውም ለአዲሱ አደረጃጀት የለውጥ ሐዋርያነት ግንባር ቀደም ሆነን የቤተ ክርስቲያኒቱን ታሪካዊነት፣ ጥንታዊነትና ሉዐላዊነት አስከብረን የቀደመ ስሟን አስመልሰን ሀብቷንና ንብረቷን በሕጋዊ አሠራር ተቆጣጥረን በአግባቡ በሥራ ላይ ለማዋል ይቻል ዘንድ በየደረጃው ያለን ሁላችንም አገልጋዮች የለውጥ ሰው ለመሆን፣ ለውጡን አምኖ ለመቀበል ሥልጠና በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዋናነት ይህን ዓላማ ከማስተግበር አንጻርም የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ለለውጡ አመራር ራሳቸውን በማስቀደም ከዚህ በፊትም ለመላው የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት ሠራተኞች ሥልጠና እንዲሰጥ ማድረጋቸውን አስታውሰው፤ የዛሬውም ከዚያ ጋር ተያያዥነት ያለው ሆኖ በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት እና ለተመደቡት አገልጋዮች በየደረጃቸው የተዘጋጀ ሥልጠና በመሆኑ ተሳታፊዎችም በሥልጠናው ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባቸው አስምረውበታል፡፡

ቅዱስነታቸው በቃለ ምዕዳናቸው ብጹዕ ረዳት ሊቀ ጳጳሱም ሆኑ ከክቡር ሥራ አስኪያጁ ጀምሮ በአጠቃላይ የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ሠራተኞች እስከ አሁን ላደረጉት የሥራ እንቅስቃሴ እና ላዘጋጁት የሥልጠና መርሐ ግብር ከፍተኛ ምሥጋና አቅርበው፤ ወደ ፊትም እንዲህ ዓይነቱ መርሐ ግብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከአደራ ጭምር ለሥልጠናው ተሳታፊ አባታዊ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡ የዕለቱ መርሐ ግብር መሪ ክቡር ዋና ሥራ አስኪያጁ መጋቤ ሀዲስ ይልማ ቸርነት የሁለቱን ቀን መርሐ ግብር አስተዋውቀው ወደ ሥልጠና ተገብቷል፡፡ የሥልጠና ርዕሶችም “የለውጥ ሥራ አመራር ሥልጠና፣ የኦዲትና ኢንስቴክሽን /ክትትልና ቁጥጥር/ ሥርዓትና ሥልጠና እንዲሁም የሒሳብ አያያዝ ሥልጠና” በሚሉ አርዕስት ሲሆን፤ ሥልጠናውም የጉባዔውን በውይይት ባሳተፈ መልኩ የሚከተሉት ነጥቦችን ዳስሷል፡-

  1.  ለውጥ በማንኛውም ተቋም ሊኖር የሚችል ክስተት መሆኑን
  2.   በለውጥ ሂደት እንቅፋቶች ለኖሩ እንደሚችሉ
  3.   ለውጥ ለአንድ ተቋም ስኬት እንደ አንድ መልካም አጋጣሚ የሚታይ መሆኑን እና ሌሎችም ነጥቦች በአቶ ታደሰ አሰፋ እና በአቶ ካሳ አወቀ
  4.  አንድ ኦዲተር ሊኖረው ስለሚገባ ሙያዊ ክህሎት
  5.   መሠረታዊ የኦዲትና ኢንስቴክሽን መርሆች
  6.  ስለ ኦዲት እና ኢንስፔክሽን ዓይነቶች እና የኦዲት ባለሙያ ስለሚያቀርበው የሪፖርት ቅርጽ በዲ/ን ንጋቱ ባልቻ እና ዲ/ን ተመስገን ወርቁ
  7.  ስለ መሠረታዊ የሂሳብ አሠራር መቅላላ ሂሳብ ሥራ መነሻ እና መድረሻ አስመልክቶ በአቶ ሞሐባ በስፋትና በጥልቀት በታዘዘላቸው ሰዓት ጊዜ ሰጥ በተሳታፊዎች የቡድን ውይይት እንዲሁም በጥያቄና መልስ ንቁ ተሳትፎ በማድግ ሥልጠናው እንዲሰርጽ አድርገዋል፡፡
  8. ከሥልጠናው የሚገኝ ግብዓት በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ከዋና ጽ/ቤቱ ጀምሮ እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት አድባራትና ገዳማት ያለውን የመልካም አስተዳደር እጦት፣ የገንዘብ እና የንብረት ብክነት፣ ያለማቋረጥ የሚታየውን የሰዎች አቤቱታ በአፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት እየተደረገ ያለው የመዋቅር ማስተካከያና ተከታታይ ሥልጠና ይበል የሚያሰኝ መልካም ጅምር ነው፡፡ ለተግባራዊነቱም በቅድሚያ በሀገረ ስብከቱና በየክፍላተ ከተሞች የምንገኝ ኃላፊዎችና ሠራተኞች በቁርጠኝነት በመነሣት፤ የነበረውን የተሳሳተ አመለካከት በፍጥነት ለመቅረፍ በእጅጉ ይረዳል ተብሎ ይታመናል፡፡ ለተግባራዊነቱም የሥልጠናው ተሳታፊዎች አዎንታዊ ምላሽ በመስጠት በተደረገው ውይይት አረጋግጠዋል፡፡ ተሳታፊውም ይህን ዓይነቱ ሥልጠና በሥራው ላይ ያለው አዎንታዊ ተጽእኖ መልካም ስለሆነ ወደ ፊትም እንዲቀጥል እየገለጸ የሚከተለውን የጋራ አቋም መግለጫ አውጥቷል፡፡

               የአቋም መግለጫ

1. እኛ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት እና የክፍለ ከተማ ጽ/ቤት ሠራተኞች ሀገረ ስብከቱ የጀመረውን የለውጥ ሥራ አመራር ሂደት ሙሉ በሙሉ በመደገፍ አዲሱን አደረጃጀት ለመተግበር ቃል እንገባለን፡፡

2. እኛ የዚህ ሥልጠና ተሳታፊዎች ለዚህ የለውጥ እንቅፋት የሚሆኑ ማንኛውም አካላትን በጽኑ በመቃወም እና በመታገል ለመልካም አሠራር ሂደት አፈጻጸም እንተጋለን፡፡

3. የክትትልና ቁጥጥር ሥራ ለአንድ ተቋም ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ተረድተን ሕግን የተከተለ የቁጥጥርና የክትትል ሥራ እንዲተገበር እንተጋለን፡፡

4. በቤተ ክርስቲያናችን ዘመናዊ የፋይናንስ ሥርዓት እንዲተገበር የበኩላችንን ሥራ እሰራለን፡፡

5. በቤተ ክርስቲያናችን ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው አሠራር እንዲሰፍን ባለንበት የሥራ ኃላፊነት ላይ ጠንክረን በመሥራት የቤተ ክርስቲያናችንን ክብር እናስጠብቃለን፡፡

6. በሀገረ ስብከቱና በክፍላተ ከተማ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን ያለመሰልቸት እንሠራለን፡፡

7. የቤተ ክርስቲያናችንን ክብርና ስም የሚያጎድፍ ብልሹ አሠራር አስወግደን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ያላትን ጥንታዊነት፣ ታሪካዊነትና ሐዋርያዊነት ለማስጠበቅ ከመቼውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ በታማኝነት ለማገልገል ቃል እንገባለን፡፡

8. ጊዜው በሚጠይቀው መሠረት የሥራ አመራር ለውጥ ለቤተ ክርስቲያችን ተልዕኮ መሳካት የሚሰጠውን ጥቅም በመረዳት ጠንክረን እንሠራለን፡፡

9. የኦዲትና ኢንስፔክሽን አገልግሎት ከማንኛውም አስተዳደራዊ ተጽዕኖ ነጻ ሆኖ ሙያዊ ተግባሩን እንዲያከናውን እንደግፋለን፡፡

10. በሂሳብ አያያዝ ሥራ በኩል ያለውን ክፍተት በማረም በተሰጠን ሥልጠና መሠረት ዘመኑ በሚጠይቀው የፋይናንስ ሥርዓት ለማስተካከል እና ለመሥራት ጥረት እንናደርጋለን፡፡

ማጠቃለያ በተለይ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትያርክ ረዳት ሊቀ ጳጳስ እና የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሥልጠናው ከተጀመረበት ደቂቃና ሰዓት ጀምሮ በቦታው ከተሳታፊዎች ቀድመው በመገኘት ለሁሉም ሠራተኞች የአባትነት አርአያነታቸውን ያሳዩን በመሆናቸው እጅግ ምሥጋናችን የላቀ ነው፡፡

እኛም የሀገረ ስብከትና የክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ሠራተኞች የብፁዕነታቸውን ፈለግ በመከተል በየተመደብንበት የሥራና የአገልግሎት ክፍል በርትተን ለመሥራት ከብፁዕነታቸው በተግባር የተተረጎመ ትልቅ የሥራ መመሪያ አግኝተናል፡፡

ብፁዕ አባታችን! እኛ ልጆችዎት ሌሊት ከቀን እየደከሙበት ያለውን የሥራ አመራር ለውጥ እና መዋቅር ተግባራዊ እንዲሆን ከልብ እንሠራለን፡፡

“አንትሙ ውእቱ ብርሃኑ ለዓለም ከማሁኬ ይብራህ ብርሃንክሙ በቅድመ ሰብእ ከመ ይርአዩ ምግባሪክሙ ሰናየ ወይሰብህዎ ለአቡክሙ ዘበሰማያት፤

የዓለም ብርሃን እናንተ ናችሁ እንዲሁ ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ በጎ ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን ያመሰግኑ ዘንድ” ማቴ. 5፡12

እኵት እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ ዘዘልፈ የአቅበነ ዘአውትሮ የሚጠብቀን የአባቶቻችን አምላክ ይመስገን አሜን!!

ነሐሴ 23 ቀን 2003 ዓ.ም አዲስ አበባ

በመጨረሻም ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት እና በሥሩ ለሉ 7 ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት የሥራ ኃላፊዎች እና ሠራተኞች ሥልጠና ተሰጠ በመዝጊያ ፕሮግራሙ ላይ የተገኙት ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የቅዱስ ሲኖዶስ ፀሐፊ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ሥልጠናው ወደ ቀደመው ታሪካችን የሚወስድ ታሪካዊ ጉባኤ ነው ብለውታል የመጀመሪያ መሪ አባት በመሆንዎ ደስ ሊሎት ይገባል በማለት ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትያርክ ረዳት ሊቀ ጳጳስ እና የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስን አመስግነዋቸዋል፡፡

የሐዋሪያት ቁልፍ የተረከብነው እኛ በመሆናችን ታሪካችን በአግባቡ ልንጠብቅ ይገባል ብለዋል፡፡ በመቀጠል ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ የመጨረሻ የመዝጊያ ንግግር እንዲያደረጉ፤ቃለ ምዕዳንና መመሪያ እንዲሰጡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የጋበዙ ሲሆን ቅዱስነታቸውም ቅዱስ ዮሐንስ አባጣ ጎርባጣውን አቅኑ እንዳለው ሁሉ እናንተም ይህን ልታቀኑ ይገባችኋል ብለዋል፡፡

ችግር ወጥቶ ካልተነገረ መፍትሔ አይመጣም እኛ ለመደበቅ ብንሞክርም ሊሆን አይችልም እናንተም በዚሁ ቆይታችሁ ብዙ እንደተወያያችሁ ይገባኛል፡፡አባቶቻችን በየዘመናቱ በሚችሉት ሲጠቀሙ ቆይተው አሁን ያለንበት ዘመን ላይ ደርሰናል ዘመኑም የኮምፒውተር እና የቴክኖሎጂ ዘመን በመሆኑ እኛም ዓለም እየተጠቀመበት ያለውን ቴክኖሎጂ በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል፤ከዘመኑ ጋር ልንራመድ እና አሠራራችን ኮምፒውተራይዝድ ሊሆን ይገባል በማለት ሰፋ ያለ ንግግር እና ቃለ ምዕዳን የሰጡ ሲሆን በመጨረሻም ለ2 ቀን ሲካሄ የቆየውን ጉባኤው በፀሎት ዘግተዋል፡፡

ለተጨማሪ ንባብ እዚህ ላይ ይጫኑ (‹‹የለውጥ ሥራ አመራር ሥልጠና››)

ለተጨማሪ ንባብ እዚህ ላይ ይጫኑ (‹‹የኦዲት እና ኢንስፔክሽን አገልግሎት››)

 
የብፁዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ የ1ኛ ዓመት መታሰቢያ የፀሎት ስነ ሥርዓት ተካሄደ

0021

ከዚህ ዓለም በሞተ ሥጋ የተለዩት የ5ኛው ፓትርያርክ የብፁዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዝደንት፣ የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዝዳንት ኅልፈት የአንደኛ ዓመት መታሰቢያ ሥነ ሥርዐት ነሐሴ 10 ቀን 2004 ዓ.ም በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በማሕሌት፣ በጸሎተ ፍትሐትና በቅዳሴ ታስቦ ውሏል፡፡በመታሰቢያ ክብረ በዓሉ ላይ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፤ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ፤ ካህናትና ምእመናን የተገኙ ሲሆን በቅዱስነታቸው መሪነት ሙሉ ፀሎተ ፍትሐት ከደረሰ በኋላ ከሰዓት ፀሎተ ቅዳሴው ተከናውኗል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በ20 ዓመት የፕትርክና ዘመናቸው ለሀገራቸውና ለዓለም ያበረከቱት አስተዋፅኦ ከፍተኛ እንደነበር በዚሁ የመታሰቢያ መርሃ ግብር ላይ ተገልጿል፡፡ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የአንደኛ ዓመት መታሰቢያ የፀሎት ስነ ሥርዓት በመንበረ ጸባዖት ቅድስተ ሥላሴ ካቴድራል ባለው መካነ መቃብራቸው ላይ ተካሂዷል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ሐምሌ 1984 ዓ.ም ፓትሪያሪከ ሆነው ከተሾሙበት ጊዜ አንስቶ ለሀገር እድገትና ልማት ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማበርከት ለ20 ዓመታት ሐወርያዊ ተልእኳቸውን በመፈፀምና ከፍተኛ አገልግሎት በማበርከት ለቅድስት ቤተክርስትያንና ለሀገሪቱ ታላላቅ ሥራዎችን ሰርተው ማለፋቸው ተገልጿል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ፓትርያርክ በስነ ሥርዓቱ ላይ እንደገለፁት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ በህይወት ዘመናቸው ለትምህርት መስፋፋት፣ ለሀገርና ለዓለም ሰላም እንዲሁም የኃይማኖት መቻቻልንም በሰፊው በማስተማርና በቤተክርስትያኗ ለሀገር እድገት ጉልህ አስተዋፅኦ እንድታበረክት በማስቻል ከፍተኛውን ሚና ያበረከቱ እንደነበር ገልፀዋል፡፡

በተያያዘ ዜና የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አንደኛ ዓመት መታሰቢያ ስነ ሥርዓት ነሐሴ 14/2005 ዓ.ም በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ባለው መካነ መቃብሩ ተካሂዷል፡፡በመታሰቢያ ክብረ በዓሉ ላይ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፤ የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ሚኒስትሮች፤ ክብርት ባለቤታቸው ወ/ሮ አዜብ መስፍን ፤ ካህናትና ምእመናን በታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ መካነ መቃብር በፀሎቱ መርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተዋል፡፡ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በመታሰቢያ የፀሎት መርሐ ግብሩ ላይ ለተገኙ ምዕመናን ሠፊ የሆነ ትምህርተ ወንጌል ሠጥተዋል ፡፡

00020

 
ዝርዝር ፅሁፍ...
<< ጀምር < ወደኋላ 1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 ወደፊት > መጨረሻ >>

ገጽ 10 ከ 20

የቤተክርስቲያን አድራሻ

የካቴድራሉ ሰበካ ጉባዔ ጽ/ቤት
ስልክ ፤ 011-1-23-35-18 / 011-1-23-35-15
አዲስ አበባ
ኢትዮጵያ
church@trinity.eotc.org.et
www.trinity.eotc.org.et

ግጻዌ

ማስታወቂያ

ለመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እድሳት የበኩልዎን አስታዋጽዖ ያድርጉ!

መርዳት የምትፈልጉ ምዕመናን ሁሉ የሚከተለውን አድራሻ መጠቀም ትችላላችሁ፡፡

አራት ኪሎ ቅርንጫፍ, ቁጥር= 0171859072600/2637 (መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እድሳት )

ብላች መላክ ትችላላችሁ፡፡