ቅ. ሥላሴ ካቴድራል

{gallery}pic-cathedral{/gallery}

ቅ. ሥላሴ ካቴድራል

{gallery}pic-cathedral{/gallery}

ቅ. ሥላሴ ካቴድራል

{gallery}pic-cathedral{/gallery}

ቅ. ሥላሴ ካቴድራል

{gallery}pic-cathedral{/gallery}

http://www.trinity.eotc-churches.org/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/46016501.jpg http://www.trinity.eotc-churches.org/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/7472451.jpg http://www.trinity.eotc-churches.org/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/395795church_4.jpg http://www.trinity.eotc-churches.org/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/357816church_5.jpg
የካቴድረሉ ዋና አስተዳዳሪ ሆነው የተሾሙት ክቡር ሊቀ ስልጣናት አባ ገ/ሥላሴ በላይ ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው

0022

በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት መልካም ፈቃድ ከነሐሴ 1 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም. ጀምሮ  የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ዋና አስተዳዳሪ ሆነው የተሾሙት ክቡር ሊቀ ስልጣናት አባ ገ/ሥላሴ በላይ ሲሆኑ ሐሙስ ነሐሴ 1 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም. የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሰበካ ጉባዔ አባላት፣መላው ማህበረ ካህናት፣ መዘምራን፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችና የአጥቢየው ምእመናን  ደማቅ አቀባበል አድርጐላቸዋል፡፡

ክቡር ሊቀ ስልጣናት አባ ገ/ሥላሴ በላይ በካቴድራሉ ሲሾሙ አሁን ለ2ኛ ጊዜ ሲሆን ቀደም ሲል ከ2004 እስከ 2005 ዓ.ም ካቴድረሉን ባስተዳደሩበት ጊዜ ብዙ ሥራ እና መልካም አስተዳደር ከማስፈናቸውም በላይ ለካቴድራሉ መንፈሳዊ እና ለሁለንተናዊ አገለግሎት የሚሆን ብዙ ገንዘብና ጥሬ እቃ ካሰባሰቡ በኋላ በደብረ ገነት መካኒሳ ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል ማህበረ ካህናትና ማህበረ ምእመናን ጥያቄ አማካኝነት ለ1 ዓመት ያህል ወደ መካኒሳ ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል ሄደው ዘርፈ ብዙ ልማት ካለሙ  በኋላ ልክ በ1 አመታቸው በካቴድራሉ ማህበረ ካህናት እና ልይ ልዩ ሠራተኞች ጥያቄና በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት መልካም ለ2ኛ ጊዜ የካቴድራሉ ዋና አስተዳዳሪ ሆነው ተሹመው መጥተዋል፡፡ክቡር ሊቀ ስልጣናት አባ ገ/ሥላሴ በላይ ወደ ካቴድራሉ በድጋሚ እንዲመጡ የተመረጡበት መክንያት መንፈሳዊና የልማት አባት በመሆናቸው ሲሆን ከአሁን በፊት የሠሯቸው ሥራዎች ትላልቅ ማረጋገጫዎች ናቸው፡፡


በክብረ በዓሉ ላይ ብፁዕ አቡነ አረጋዊ የካቴድራሉ የበላይ ጠባቂና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ፤የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች  ፤የደብረ ገነት መካኒሳ ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል ካህናት፤የካቴድራሉ ማህበረ ካህናትና ልይ ልዩ ሠራተኞች በክብረ በዓሉ ላይ ተገኝተዋል፡፡ በዓሉን አስመልክቶም የተለያዩ ቅኔዎችና ዝማሬዎች በካቴድራሉ ሊቃውነት  አማካኝነት ቀርቧል፡፡
በስተመጨረሻ የተደረገላቸውን አቀባበል በማስመልከት ንግግር ያደረጉት ክቡር ሊቀስልጣናት አባ ገ/ሥላሴ በላይ ሲሆኑ የተደረገላቸውን አቀባበል ካመሰገኑ በኋላ ካቴድራሉ ዓለም አቀፋዊ እንደመሆኑ መጠን በልማትና በመልካም አስተዳደር ወደተሻለ ደረጃ ላይ እንዲደርስ የሁሉም ሠራተኛ እና ምእመናን አስተዋጽኦ ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ከዚሁ ጋር አያይዘውም ዘመኑ በሚፈቅደው አስተሳሰብና አሰራር ሰዎች መሥራት ይኖርብናል ብለዋል፡፡ ሥርዓተ ቅዳሴው በክቡር ሊቀ ስልጣናት አባ ገ/ሥላሴ በላይ መሪነት ከተከናወነ በኋላ የበዓሉ ፍፃሜ ሆኗል፡፡
መልካም የሥራ ዘመን እንዲሆንላቸውም ሁሉም የካቴድራሉ ሠራተኞች ተመኝተውላቸዋል፡፡

 
ዓመታዊው የዓጋዕዝተ ዓለም ሥላሴ ክብረ በዓል በድምቀት ተከበረ

g0027

በየዓመቱ ሐምሌ 7 ቀን በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የሚከበረው ዓመታዊው የሥላሴ በዓል በዚህ ዓመትም በመንበረ ጸባዖት ቅድሰት ሥላሴ ካቴድራል ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኩሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ ብፁአን ሊቃነ ጳጳሳት እንዲሁም በብዙ ሽህ የሚቆጠሩ ምዕመናን በተገኙበት እጅግ በጣም ደማቅ በሆነ ሁኔታ በዓሉ ተከብሮ ውልዋል፡፡
በዚሁ ዕለት አጋዕዝተ ዓለም ሥላሴ በአብርሃም ቤት ተገኝተው ቤቱን የባረኩበት፣ የአንድነታቸውንና ሶስትነታቸው ሚስጢር የተገለፀበት ታላቅ በዓል ነው። በዓሉ መከበር የጀመረው ከዋዜማው ከሐምሌ6 ጀምሮ ሲሆን የካቴድራሉ ካህናትና መዘምራን ከዋዜማው ከቀኑ 3 ሰዓት ጀምሮ ለ30 ሰዓታት ያህል ሌሊትና ቀኑን ሙሉ ያለ ማቋረጥ ስብሃተ እግዚአብሔር ሲያቀርቡ ውለው አድረዋል፡፡
ይህመንፈሳዊ አገልግሎት ማለትም ስርዓተማህሌተ፣ ስርዓተቅዳሴ እንዲሁም ሰዓታትና ሰርክ ፀሎት በአጠቃለይ የስርዓተ አምልኮ አፈፃፀም በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ልዩ በመሆኑ የእምነቱ ተከታዮች ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም እጀግ በጣም የሚያስደንቅ በዓል ነው፡፡በክብረ በዓሉ ላይ የተገኙት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኩሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ሥርአተ ቅዳሴውን የመሩት ሲሆን በካቴድራሉ አውደ ምህረት ላይ ተገኝተውም  በአሉን ለማክበረ ከተለያየ ቦታ ለመጡ ምዕመናን በዓሉን አስመልክተው ሰፋ ያለ ትምህርተ ወንጌል ሰጥተዋል፡፡

 
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የ2006 ዓ.ም.የትንሣኤ በዓልን አስመልክቶው ቃለ ምዕዳን አስተላለፉ

0908

ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት
በእንተ ትንሣኤሁ ለእግዚእነ ወአምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
•    በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣
•    ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምኖሩ፣
•    የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፣
•    በሕመም ምክንያት በየሆስፒታሉ ያላችሁ፣
•    እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት በሙሉ፤
እርሱ ሕያው ሆኖ ሕያዋን መሆናችንን በትንሣኤው ላበሠረን ለጌታችን  ለአምላካችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ትንሣኤ እንኳን በሰላም አደረሳችሁ!!
‹‹ወርኢናሃ ለሕይወት፤ ወተዐውቀት ለነ፤
ሕይወትን አየናት፣አወቅናትም›› (1ዮሐ1÷2)
የሕይወት መገኛና ምንጭ አምላካችን እግዚአብሔር ነው፣ ከእግዚአብሔር የተገኘው ሕይወት የሰው ልጅ የዕውቀት ብርሃን ነው፤ አምላካዊ ሕይወት ካለው ሰው የሚፈልቅ ብርሃናዊ ዕውቀት ጽልመታዊውን ዓለም በብሩህነቱ ያሸንፋል እንጂ በጽልመታዊ ዓለም አይሸነፍም፡፡ (ዮሐ.1÷4-5)
    የሰው ልጅ ሕያው አምላክ በመልኩና በአምሳሉ የፈጠረው ፍጡር በመሆኑ  ሕያውና ክቡር፣ ዘላለማዊና ብርሃናዊ፣ የማሰብ፣ የማመዛዘን፣ የመምረጥና፣ የመወሰን ነጻነት ያለውና ከሌሎች ፍጥረታት ሁሉ የላቀ አእምሮ ያለው ልዑል ፍጡር ነው፤
    ሰው ከእግዚአብሔር በተሰጠው ነጻነትና አእምሮ መሠረት ነጻነቱን ተጠቅሞ የመረጠውን የማድረግ ነጻነት ያለው ፍጡር ቢሆንም በነጻ ዕውቀቱና ምርጫው ለሚፈጽመው ሁሉ እርሱ  ራሱ ኃላፊነቱን ይወስዳል፤
ይህም ማለት በምርጫው መሠረት የሚሠራው ሥራ ሁሉ በእውነተኛው ዳኛ በእግዚአብሔር ፊት መልካም ሆኖ ከተገኘ ምስጋናን፣ መልካም ሆኖ ካልተገኘ ግን ተጠያቂነትንና ፍርድን ያስከትልበታል ማለት ነው፡፡
ከዚህ አንጻር የመጀመሪያ ሰው የሆነው አዳም ማድረግ ያለበትንና ማድረግ የሌለበትን ተለይቶ ከእግዚአብሒር ቢነገረውም የተነገረውን ሕግ ወደጎን ገሸሽ በማድረግ የራሱን ነጻ ምርጫ ተጠቅሞ ‹‹አትብላ›› የተባለውን በላ፤
በመሆኑም ይህ ድርጊት በእግዚአብሔር ዘንድ እጅግ ታላቅ ስሕተትና ድፍረት  ነበረና ተጠያቂነትን አስከተለ፣ በመጨረሻም ሕይወትን የሚያሳጣ የሞት ፍርድንና ቅጣትን በራሱና በልጆቹ ሁሉ ላይ አመጣ፡፡
ፍርዱ ሥራ ላይ ከዋለበት ቀን ጀምሮ ሰው ሕይወቱን አጣ ማለትም ከእግዚአብሔር አንድነት ተለየ፤ ሞትና ሲኦልም ሰውን ከእግዚአብሔር ለይተውና የራሳቸው ተገዥ አድርገው እስከ ስቅለተ ክርስቶስ ድረስ በቁጥጥራቸው ሥር አዋሉት፡፡
ሆኖም እግዚአብሔር በባህርዩ መሐሪና ፈራጅ እንደመሆኑ መጠን ለፈራጅነቱና ለመሐሪነቱ የሚስማማ መንገድ አመቻችቶ መሐሪነቱንና ፈራጅነቱን በፈጸመበት በክርስቶስ ሞት ቤዛነት የሰው ልጅን ታረቀው፤ ያጣውንም ሕይወት መለሰለት፤ በምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አማካኝነትም እንደገና ሕይወቱን እንዲያገኝ አደረገ (ዮሐ. 6÷56-58፤ ማር 16÷16)
    ይህን አስመልክቶ ቅዱስ ጳውሎስ ሲናገር‹‹በመጀመሪያው ሰው (አዳም) ሞት መጣ፣ በሁለተኛው ሰው (ክርስቶስ) ግን ትንሣኤ ሙታን ሆነ፤ሁሉም በአዳም እንደሚሞቱ እንደዚሁ ሁሉም በክርስቶስ  ሕያዋን ይሆናሉ›› ብሏል፤ (1ቆሮ 15÷21-22፤ሮሜ 5-12-19)
ከዚህ የምንረዳው ዓቢይ ቁም ነገር በአዳም አለመታዘዝ ምክንያት ያጣናት ሕይወት፣ በክርስቶስ መታዘዝ ያገኘናት መሆናችንን ነው፤ ጌታችንም ‹‹ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ ሕያው የሆነም፣ የሚያምንብኝም፣ ሁሉ ለዘላለም አይሞትም፤እኔም በመጨረሻይቱ ቀን አስነሣዋለሁ›› ብሎ ትንሣኤና ሕይወት መሆኑን እንደነገረን የሰው ልጅን ለዘላለማዊ ሕይወት እንደገና አበቃው (ዮሐ. 6÷54፤ 11÷25-26)
የዚህም እውነታ በትንሣኤው አበሰረን፣ የእርሱ ትንሣኤ የትንሣኤያችን ዋዜማ ነውና የቀደመችው ሕይወት እንደተመለሰችልን በትንሣኤው አየናት፤ አወቅናትም፤(ኤፌ.4÷5-7)
        የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼ ምእመናንና ምእመናት
     የክርስቶስ ትንሣኤ ለሰው ልጅ የዘላለማዊ ሕይወት ማረጋገጫ ነው፤ለበርካታ ዘመናት በተስፋ ይጠበቅ የነበረው የክርስቶስ ነገረ አድኅኖ እና ነገረ ትንሣኤ በጊዜው ጊዜ እውን እንደሆነ ሁሉ፣ እንደዚያው በተስፋና በእምነት እየተጠባበቅነው ያለ የሰው ልጅ ሕይወታዊ ትንሣኤ ጊዜው ሲደርስ በክርስቶስ ዳግም ምጽአት እውን ይሆናል፤(1ቆሮ 15÷20-23፤1ተሰ 4÷13-18)
 ይሁን እንጂ ዛሬም ሕይወትን በሚሰጥ በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ያለን ስለሆን የሕይወትን ጣዕም አሁንም ማጣጣም እንችላለን፤ ሕይወት ጣዕም የሚኖረው በፍቅር ሲታጀብ ነው፣ ፍጹም ፍቅር የዘላለማዊ ሕይወት ኃይል ነው፤ ፍቅር ፍጹም የሚሆነው ሦስቱን አቅጣጫዎች ማእከል አድርጎ ሲገኝ ነው፤
 ይኸውም ወደ ላይ እግዚአብሔርን በፍጹም ፍቅር መከተል ስንችል፣ ወደጎን በአርአያ እግዚአብሔር የተፈጠረውን የሰው ልጅ በአጠቃላይ መውደድ ስንችል፣ ወደ ታች ደግሞ የምንኖርባትን ምድርና በውስጧ ያሉ ፍጥረታትን ስንንከባከብ ነው፣ ይህን ካደረግን ፍጹም ፍቅር ከእኛ  አለ ማለት እንችላለን፤ እግዚአብሔር ይህንን ዓይነት ፍቅር እንዲኖረን በሃይማኖት አስተምሮናል፡፡
    በመሆኑም እኛ ክርስቲያኖች ለእግዚአብሔር ያለንን ፍቅር ለመግለጽ በመዋዕለ ጾሙ በአምልኮ፣ በጾም፣ በጸሎት፣ በምጽዋትና በስግደት ስንገልጽ እንደቆየን ሁሉ፣ በፋሲካው በዓላችን እግዚአብሔር የሰጠንን በረከት ከተቸገሩ ወንድሞቻችንና እኅቶቻችን ጋር በመካፈል ለወገኖቻችን ያለንን ፍቅር ልንገልጽ ይገባናል፤
በዚህ ዕለት በዓሉን ስናከብር የተራቡትን በማብላት፣ የተጠሙትን በማጠጣት፣ የታረዙትን በማልበስ፣ ጧሪ የሌላቸው አረጋውያን፣ አሳዳጊ የሌላቸው ሕጻናት፣ በልዩ ልዩ ምክንያት የአካልና የአእምሮ ጉዳት ደርሶባቸው የበይ ተመልካች የሆኑ ወገኖች ሁሉ ከእኛ ጋር በማዕዳችን ተሳታፊ ሆነው በዓሉን በደስታና በምስጋና እንዲያከብሩ ማድረግ ክርስቲያናዊ ግዴታችን ነው፡፡
            የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼ ምእመናንና ምእመናት
የትንሣኤ መሠረታዊ ትርጉም ከሞት በኋላ በሕይወት መኖርና መመላለስ ነው፤ ስለሆነም የትንሣኤን በዓል ስናከብር ባለፉት ዘመናት በድህነትና በኋላ ቀርነት ከሞት አፋፍ ደርሳ የነበረችውን ሀገራችን በልማትና በዕድገት ትንሣኤዋን ለማረጋገጥ ቃል በመግባት በዓሉን ማክበር ሀገራዊ ብቻ ሳይሆን ሃይማኖታዊ ግዴታ መሆኑን መገንዘብ አለብን፤
 ምክንያቱም ጠንክረን በመሥራት ምድራችንን እንድናለማና እንድንከባከብ ከሁሉ በፊት ያዘዘ እግዚአብሔር ነውና፤ በተለይም የልማታችን የጀርባ አጥንት ሆኖ እንደ ሚያገለግል ታላቅ ተስፋ የተጣለበት ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በተያዘው ፍጥነት ሥራው ተሠርቶና ተጠናቆ የዕድገታችን ተሸካሚ ምሶሶ ሆኖ ማየት እንድንችል ሁሉም ኢትዮጵያዊ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ቤተ ክርስቲያናችን ጥሪዋን ታስተላልፋለች፤
    የሀገራችን የልማትና የዕድገት መርሐ ግብሮች ዘርፈ ብዙ እንደመሆናቸው መጠን ገበሬው በየአካባቢው እያከናወነው የሚገኝ አፈርን የመገደብና አካባቢን በአረንጓዴ ልማት የማስዋብ ሥራ ያለመቋረጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በማድረግ ረገድ ቤተ ክርስቲያችን በግባር ቀደም ተሰልፋ እንደምትሠራ በዚህ አጋጣሚ ለማረጋገጥ እንወዳለን፡፡
    በአሁኑ ጊዜ በሥራ ላይ ያሉም ሆኑ ወደፊት ሊሠሩ በእቅድ የተያዙ የሀገራችን የልማትና የእድገት ሥራዎች በሕዝቡ የተባበረ ድጋፍ ሲከናወኑ የሀገራችን ብልጽግና እውን እንደሚሆን የሁላችንም እምነት ነው
ስለሆነም ለዚህ ስኬት የኢትዮጵያውን ሁሉ ጽናት፣ አንድነት፣ ስምምነትና ፍቅር፣ ሰላምና ተቻችሎ መኖር የማይተካ ሚና እንዳላቸው ለአፍታ እንኳ መዘንጋት የለብንም፤
          የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼ ምእመናንና ምእመናት
ልማታችን በተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ ብቻ ሳይሆን የተቀደሰውና የተከበረው ባህላችንና ሰብኣዊ ሥነ ምግባራችንን ጠብቆ በማስጠበቅ ጭምርም መሆን ይገባዋል
ኢትዮጵያ ሀገራችን ከጥንት ጀምሮ በቅዱሳት መጻሕፍት ሀገረ እግዚአብሔር ነች ተብሎ በተደጋጋሚ የተነገረላት ያለምክንያት አልነበረም
ኢትዮጵያውያን አባቶቻችን በማናቸውም ጊዜ ከነውረ ኃጢአትና ከርኩሰት ሁሉ ርቀው፣ ሕገ ተፈጥሮንና ሕገ እግዚአብሔርን ጠብቀው፣ እግዚአሔር የሚለውን ብቻ አዳምጠውና አክብረው የሚኖሩ ቅዱሳን በመሆናቸው እንጂ
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ምድር ሊፈጸም ቀርቶ ሊወራ የማይገባውን ሰዶምንና ገሞራን በእሳት ያጋየ ግብረ ኃጢአት በኢትዮጵያ ምድር መሰማቱ እግዚአብሔር ለኢትዮጵያውያን የሰጠውን የቅድስና ክብር የሚያሳጣ ከመሆኑም ሌላ በሀገራችን ላይ ልማትና ዕድገት ሳይሆን መቅሰፍትና ውድቀት እንዳያስከትልብን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ይህንን የሰዶም ግብረ ኃጢአት በጽናት መመከት አለበት፤
ተፈጥሮን ለማልማት እየተረባረብን እንደሆነ ሁሉ ከዚህ ባልተናነሰ ሁኔታ የሰዶም ግብረ ኃጢአትን በመከላከል በቅዱስ ባህልና ሥነ ምግባር እጅግ የበለፀገና የለማ ትውልድ ማፍራት የልማታችን አካል ማድረግ አለብን፤
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ይህንን ግብረ ኃጢአት እስከ መጨረሻው ድረስ አምርራ የምትዋጋው መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ለመላው ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ማረጋገጥ እንፈልጋለን፤  ስለሆነም ሕዝባችን ለሰላምና ለአንድነት፣ ለእኩልነትና ለልማት፣ ለቅዱስ ባህልና ሥነ ምግባር ቅድሚያ ሰጥቶ በሁሉም አቅጣጫ ልማቱን እንዲያፋጥን፣ ሃይማኖቱንም እንዲጠብቅ መልክታችንን እናስተላልፋለን፡፡
መልካም የትንሣኤ በዓል ያድርግልን!!
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝባችንን ይባርክ  ይቀድስ አሜን !!

አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖ
ሚያዝያ 12 ቀን 2006 ዓ.ም
አዲስ አበባ

 
ዕለታተ ሰሙነ ሕማማት

ሰሙነ ሕማማት ምንድን ነው?

ከዕለተ ሆሣዕና ሰርክ እስከ ትንሣኤ ሌሊት ያለውን ጊዜ ወይም ቀናት የሚያመለክት ነው፡፡ ሐመ ማለት ታመመ ማለት ሲሆን ይህም የሰውን ዘር ሁሉ ከዲያብሎስ ባርነት ነፃ ለማውጣት ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፈቃዱ የተቀበላቸውን ጸዋትወ መከራዎች የሚያሳስብ ነው፡፡ ዕለታቱ የዓመተ ኩነኔ ወይም የዓመተ ፍዳ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ክርስቲያኖች የክርስቶስን ውለታ እያሰቡ እጅግ የሚያዝኑበት፣ የሚያለቅሱበት፣ የሚሰግዱበት ቤት ንብረታቸውን ትተው ከሌላው ቀናትና ጊዜያት በተለየ መልኩ ቤተ ክርስቲያናቸውን የሚማጸኑበት፤ ጧት ማታ ደጅ የሚጠኑበት፤ ኃጢአታቸውን በቤተ ክርስቲያን አደባባይ ለካህኑ የሚናዘዙበት በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የሚገኝ ሳምንት ነው፡፡ በዚህ ሳምንት በመራብ በመጠማት በመውጣት በመውረድ በመስገድ በመጸለይ በመጾም በየሰዓቱ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ጸዋትወ መከራዎች በማሰብ አብዝቶ ይሰገዳል፡፡ መከራውን፣ ሕማሙን፣ ድካሙን የሚያስታውሱ ከቅዱሳት መጻሕፍት ኢሳይያስ፣ ኤርምያስ መዝሙረ ዳዊት ግብረ ሕማማት ወዘተ በየሰዓቱ ይነበባል፡፡ መስቀል መሳለም የለም፡፡ ካህናትም እግዚአብሔር ይፍታህ አይሉም የሳምንቱ ሥርዓተ ፍትሐት አይደረግም፡፡ ይኸውም ይህ ሳምንት ከሞት ወደ ሕይወት የተሸጋገርንበት ከጨለማ ወደ ብርሃን የተጓዝንበት የመሸጋገሪያ ወቅት ምሳሌ በመሆኑ ነው፡፡ በዕለተ ምጽአት መላእክት የመለከት ድምጽ በማሰማት የዳግም ምጽአትን ዕለት ለማሳሰብ ምእመናን ጥሪውን ሰምተው ለዚህም አስቀድመው ተዘጋጅተው የበዓሉ ታዳሚዎች መሆናቸውን በማጠየቅ በዚህ ሳምንት ዲያቆኑ ቃጭል እየመታ በየሰዓቱ ምእመናኑን ያሳስባል፡፡

በሰሙነ ሕማማት የሚገኙ ዕለታትና ስያሜያት

ዕለተ ሰኑይ /ሰኞ/ ይህ ዕለት አንጾሖተ ቤተ መቅደስ /የቤተ መቅደስ መንጻት/ እና መርገመ በለስ የተፈጸመበት ዕለት ነው፡፡ /ማር.11-11፣ ማቴ.21-18-22 ሉቃ.13-6-9/፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ «ወመሰለ ሎሙ ወይቤሎሙ አሐዱ ብእሲ በለሰ ቦቱ ውስተ አጸደ ወይኑ ወየሐውር ይንሣእ ፍሬሃ ወኢይረክብ ...»፤ ይህንም ምሳሌ አለ ለአንድ ሰው በወይኑ አትክልት የተተከለች በለስ ነበረችው ፍሬም ሊፈልግባት ወጥቶ ምንም አላገኘም፡፡ በማለት በበለስ ስለተመሰለ የሰው ልጅ ሕይወት በማሰብ እንዲመለስ ንስሐ እንዲገባ በሕይወትም እንዲኖር እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ማሳሰቡን ያጠይቃል፡፡ ንስሐ አልገባም አልመለስም ያለም በለሷ እንደጠወለገችና እንደተቆረጠች ሁሉ ፍሬ ባለማፍራታቸው እንደሚቆረጡ እንዲሁም ወደ እሳት እንደሚጣሉ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያስረዳል፡፡ በለስ የተባለች ቤተ እስራኤል ፍሬ የተባለ ደግሞ ሃይማኖትና ምግባርን ነው፡፡ ሁላችን ቤተ እስራኤላውያን ፍሬ ሃይማኖት ወምግባር አስተባብረን ይዘን መገኘት ይገባናል፡፡ ፍሬ አልባ እንዳንሆን ጌታ ሲመጣም እንዳናፍር የመጽሐፉን ቃል ልንጠብቅና ልንፈጽም ይገባናል፡፡ በዚህ የሕማማት የመጀመሪያ ቀን ዕለተ ሰኑይ የምናስበው የምንዘክረው የሰው ልጅ ሕይወት በከንቱ በቸልተኝነት እንዳይደክም እንዳይጠወለግ እንዳይደርቅ ወደ እሳትም እንዳይጣል ማድረግ ይገባናል፡፡

ዕለተ ሠሉስ /ማክሰኞ/ ይህ ቀን ጌታችን ሰኞ በተናገረውና ባደረገው ላይ አይሁድ ጥያቄ ያቀረቡበት እርሱም መልስ በመስጠት ያስተማረበት ዕለት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የጥያቄ እና የትምህርት ቀን በመባል ይታወቃል፡፡ ጥያቄውም ጌታ ባደረገው አንጽሖተ ቤተ መቅደስ ምክንያት ለጸሐፍትና ፈሪሳውያን ይኸውም ትምህርት ማስተማር፣ ተአምራት ማድረግ፣ ገበያ መፍታትን በማን ሥልጣን ታደርጋለህ? ይህንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ?» የሚል ነበር፡፡ /ማቴ.21-23-27/፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ማቴዎስ «ወይቤሎሙ ኢየሱስ አማን እብለክሙ ከመ መጸብሓውያን ወዘማውያት ይቀድሙክሙ ውስተ መንግሥተ እግዚአብሔር»፤ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው እውነት እላችኋለሁ ቀራጮችና ጋለሞቶች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በመግባት ይቀድሙአችኋል ሲል አስተምሯል፡፡ /ማቴ.21-28/

ዕለተ ረቡዕ ይህ ዕለት ደግሞ የአይሁድ ሊቃነ ካህናትና ጸሐፍት ጌታን እንዴት መያዝ እንደሚችሉ ምክር የጀመሩበት ቀን ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ዕለቱ የምክር ቀን በመባል ይጠራል፡፡

ዕለተ ሐሙስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዕለት ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ መሆኑን ለመግለጥ እና ለአርአያነት ጸሐፍት ፈሪሳውያን የአይሁድ ካህናት መጥተው እስኪይዙት ድረስ ሲጸልይ በማደሩ ምክንያት ጸሎተ ሐሙስ በመባል ይታወቃል፡፡ ትሕትና ፍቅር መታዘዝ እንዲሁም የአገልግሎትን ትርጉም ለማስረዳትና ለማስገንዘብ የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠቡ ሕጽበተ ሐሙስ በመባልም እንደሚጠራ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ይናገራሉ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስም «ወሶበ ኀፀቦሙ እገሪሆሙ ነሥአ አልባሲሁ ወረፈቀ ካዕበ ወይቤሎሙ አእመርክሙኑ ዘገበርኩ ለክሙ ... ወሶበ አነ እንከ ሊቅክሙ ወእግዚእክሙ ኀፀብኩክሙ እገሪክሙ ከማሁኬ አንትሙኒ ይደልወክሙ ትኅፅቡ እግረ ቢጽክሙ፡፡»፤ «እግራቸውንም አጥቦ ልብሱንም አንሥቶ ዳግመኛ ተቀመጠ እንዲህም አላቸው ያደረግሁላችሁን ታስተውሉታላችሁን?... እንግዲህ እኔ ጌታና መምህር ስሆን እግራችሁን ካጠብሁ እናንተ ደግሞ እርስ በእርሳችሁ ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል ሲል ተናግሯል፡፡ /ዮሐ.13-12-20/፡፡ ይህ ስለ እናንተ በመስቀል ላይ የሚቆረሰው ሥጋዬ ነው እንካችሁ ብሉ፤ ይህ ስለ እናንተ የሚፈስ ደሜ ነው ከእርሱ ጠጡ በማለት ምሥጢረ ቁርባንን የመሠረተበት ወይም ራሱ ምስጢረ ቁርባንን የጀመረበት ቀን በመሆኑ የምስጢር ቀን ተብሎ ይጠራል፡፡ ይኸውም የሰው ልጆች ሥጋውንና ደሙን ተቀብለን ከእርሱ ጋር አንድነትና ኅብረት እንዲኖረን ጥንተ ጠላት ዲለብሎስንም ፍጹም ድል ነሥተን ሰማያዊት ርስት መንግሥተ ሰማያትን እንድንወርስ ለማስቻል ነው፡፡ /ማቴ.26-26-29/፡፡ አይሁድ ጌታችንን ለመያዝ በእነርሱ ጥበብና ፍላጐት ቀስ ብለው መጥተው የያዙበት ቀን ስለሆነ በዚህ ዕለት በለሆሳስ /ብዙ የድምጽ ጩኸት ሳይሰማ/ የቅዳሴ ሥርዓት ይፈጸማል፡፡ ስለሆነም መላው ሕዝበ ክርስቲያን በዚህ የሕጽበት፣ የምስጢር፣ የጸሎት ቀን በተባለው በዚህ ዕለት በንስሓ ታጥበው ሥጋ ወደሙ እንዲቀበሉ ቤተ ክርስቲያን በአጽንኦት ታስተምራለች፡፡

ዕለተ ዐርብ ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስ «አውቀውስ ቢሆን የክብርን ጌታ ባልሰቀሉት» /1ቆሮ.1-18/፡፡ እንዳለ ይህ ዕለት የአይሁድ ካህናት ያለበደል ያለጥፋት ንጹሕና ጻድቅ የሆነውን ጌታ የሰቀሉበት ዕለት ነው፡፡ ዕለቱም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለም ሁሉ መድኃኒት ለአዳምና ለልጆቹ ሲል በመልእልተ መስቀል በቀራንዮ አደባባይ ተሰቅሎ መዋሉን የምናስብበት ታላቅ ቀን ነው፡፡ /ማቴ.27-35-75/፡፡ በዚያን ጊዜ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ እንደተፈረደበት አይቶ ተጸጸተ ሠላሳውንም ብር ለካህናት አለቆችና ለሽማግሎች መልሶ ንጹሕ ደም አሳልፌ በመስጠቴ በድያለሁ አለ፡፡ እነርሱ ግን እኛስ ምን አግዶን? አንተው ተጠንቀቅ አሉ፡፡ ብሩንም በቤተ መቅደስ ጥሎ ሔደና ታንቆ ሞተ፡፡ የካህናት አለቆችም ብሩን አንሥተው የደም ዋጋ ነውና ወደ መባ ልንጨምረው አልተፈቀደም አሉ፡፡ ተማክረውም የሸክላ ሠሪ መሬት ለእንግዶች መቃብር ገዙበት፡፡ ስለዚህ ያ መሬት እስከ ዛሬ ድረስ የደም መሬት ተባለ፡፡ /ማቴ.27-3-9/ የሰው ልጆች በዘር ኃጢአት /ቁራኝነት/ ይኖሩበት የነበረው የጨለማ ሕይወት ያከተመበት ፍጹም ድኅነት ያገኙባት ታላቅ ዕለት ናት፡፡ ክርስቲያኖች ሁልጊዜም ዕለተ ዓርብ ሲመጣ ሕማሙን ስቅለቱን ሞቱን የሚያስቡበት ጊዜ ነው፡፡ በሮማውያን ሕግና ሥርዓት መስቀል የወንጀለኞች መቅጫ ምልክት የሕይወት መቅጫ አርማ ሆኖ ሳለ ለእኛ የዲያብሎስ ድል መንሻ ስላደረገው በስቅለቱና በሞቱም ሕይወትን ስለአገኘን በዚህም ምክንያት መልካሙ ዓርብ በመባል እንደሚታወቅ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ያትታሉ፡፡

ቀዳሜ ስዑር ዕለተ ቅዳሜ እግዚአብሔር የሚታዩትንና የማይታዩትን፣ በእግር የሚሄዱትን እና በክንፍ የሚበሩትን በባሕር የሚዋኙትን እንስሳትን በመጨረሻም ሰውን በአርአያውና በአምሳሉ ፈጥሮ ያረፈበት ዕለት ነች፡፡ ይህች የመጀመሪያው ቅዳሜ ለእግዚአብሔር የዕረፍት ዕለት ናት እግዚአብሔርን ሥነ ፍጥረት ፈጥሮ ስላረፈበት ሰንበት ዐባይ /ታላቋ ሰንበት/ ትባላለች ታላቋን ሰንበት እስራኤላውያን እንዲያከብሯት ታዟል፡፡ ዘፍ.1፡3፡፡ ዕለተ ቀዳሚት /ሰንበት ዐባይ/ በዘመነ ሐዲስም የተለየ የደኅነት ሥራ ተከናውኖባታል፡፡ ጥንት ሥነ ፈጥረትን በመፍጠር ዕረፍት እንደ ተደረገባት ሁሉ የፍጥረት ሁሉ ቁንጮ የሆነውን አዳምን ለማዳን ሕማምና ሞት የተቀበለው ቸሩ አምላክ በመቃብር አርፎባታል፡፡ ማቴ.27፡61፡፡ በዚህች ዕለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በከርሰ መቃብር ዐርፎ የዋለባት ዕለት በመሆኗ «ቀዳሜ ስዑር » ትሰኛለች፡፡

ስዑር ቀዳሜ የተባለችው በዓመት አንድ ቀን ስለ ምትጾም ነው፡፡ ምክንያቱም እናቱ ድንግል ማርያም ወዳጆቹ ቅዱሳን ሐዋርያት ጌታ ተላልፎ ከተሰጠበት ዕለት አንስተው ብርሃነ ትንሣኤውን እስኪያዩ ድረስ እህል ውኃ በአፋቸው አልዞረም፡፡ ይመኩበትና ተስፋ ያደረጉት የነበረ አምላካቸው በመቃብር ስላረፈ ዕለቷን ሞቱን በማሰብ ትንሣኤውን በመናፈቅ በጾም አክብረዋታል፡፡ ከቅዱሳን ሐዋርያት ሲወርድ ሲወራረድ በመጣው ትውፊት መሠረት ቅዱሳን ሐዋርያት በማዘን በመጾምና በመጸለይ ዕለቷ እንዳከበሯት የተዋሕዶ ልጆች የተቻላቸው ከዓርብ ጀምረው የሚያከፍሉ /የሚጾሙ/ ለሁለት ቀን እህል ውኃ ሳይቀምሱ ያድራሉ ያልተቻላቸው ደግሞ ዓርብ ማታ በልተው ቅዳሜን በመጾም ትንሣኤን ያከብራሉ፡፡ በዚህ ዕለት ከሰኞ ከሆሣዕና ማግሥት ጀምረው እስከ ስቅለተ ዓርብ ድረስ በስግደት እና በጾም ያሳለፉ ምእመናን በዕለተ ቅዳሜ በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ይሰበሰባሉ፡፡ የጠዋቱ ጸሎት ሲፈጸም ካህናቱ «ገብረ ሰላመ በመስቀሉ፡-በመስቀሉ ሰላምን መሠረተ» የምሥራች እያሉ በቤተ ክርስቲያን ለተሰበሰቡት ምእመናን ቄጠማ ይታደላል ቄጠማው የምሥራች ምልክት ነው፡፡ ቄጠማው የምሥራች ምልክት ተደርጐ የተወሰደው በኖህ ዘመን ከተፈጸመው ታሪክ ጋር በማቆራኘት ነው፡፡

ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን በጻድቁ ኖኅ ዘመን የነበሩ ሕዝቦች ከሕገ እግዚአብሔር ውጪ ሆነው እጅግ የሚያሳዝን ኃጢአት በሠሩ ጊዜ በንፍር ውኃ ተጥለቅልቀዋል፡፡ በወቅቱ ጻድቁ ኖኅ ወደ መርከብ ይዞአቸው ከገባው እንስሳት መካከል የውኃውን መጉደል ለመረዳት ርግብን በመርከብ መስኮት አሾልኮ ይለቃታል፤ እርሷም ቄጠማ በአፍዋ ይዛ ትመልሳለች፡፡ ዘፍ.9-1-29፡፡ ኖኅም በዚህ ቄጠማ የውኃውን መድረቅ ተረድቶ ተደስቷል፡፡

«ቄጠማ»፣ ለጥፋት ውኃ መድረቅ የምሥራች መንገሪያ እንደሆነ አሁንም በክርስቶስ ሞት ሞተ ነፍስ ከሰው ልጆች ተወገደ ስትል ቤተ ክርስቲያን ለልጆቿ ቄጠማ ታድላለች፡፡ ምእመናንም የምሥራች ተምሳሌት የሆነውን ቄጠማ በግንባራቸው ያስሩታል፡፡ የክርስቶስ ተከታዮች ሁሉ ከጨለማ ወደ ብርሃን ከሚያቃጥለው ዋዕየ ሲኦል /የሲኦል ቃጠሎ/ ወደ ልምላሜ ገነት ጥንተ ማኅደራቸው መመለሳቸውን በዚህ አኳሃን እየገለጡ በዓለ ትንሣኤን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያከብራሉ፡፡

 
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የ2006 ዓ.ም.የ2006 ዓ.ም. ዐብይ ጾምን አስመልክቶ ቃለ ምዕዳን አስተላለፉ

0908

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የ2006 ዓ.ም. ዐቢይ ጾም አስመልክቶ እንኳን በሰላም አደረሳችሁ ባሉበት ወቅት “ጾም ለመንፈሳዊ ሕይወት መጎልበት፣ ራስን ለመግዛት፣ ከእግዚአብሔር ጋር ልዩ ግንኙነትና አንድነት ለመፍጠር እጅግ አስፈላጊ ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ቅዱስነታቸው ዐብይ ጾሙን አስመልክቶ ያስተላለፉትን ሙሉ ቃል ከዚህ በታች ይመልከቱ፡፡
መልእክት ዘእም ኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በእንተ በዓለ ጾም ዓቢይ ዘእግዚእነ ወአምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ሎቱ ስብሐት፡፡
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

በሀገር ውስጥም ኾነ በውጭ የምትኖሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንና ምእመናት የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን በሙሉ፡-
እግዚአብሔር አምላክ እንኳን ለ፳፻፮ ዓ.ም. የጌታችን የአምላካችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መዋዕለ ጾም በሰላም አደረሳችኁ፡፡
‹‹ወእመሰ በምግባረ መንፈስ ቀተልክምዎ ለምግባረ ነፍስትክሙ ተሐይዉ ለዓለም፤ በመንፈሳዊ ሥራ ሥጋዊ ሥራችኹን ብትገድሉ ለዘላለሙ ትድናላችኹ፡፡›› /ሮሜ ፰÷፲፫/
ጾም ከጥንት ጀምሮ በዘመነ ብሉይም በዘመነ ሐዲስ የተወደደ፣ የፈቃደ ሥጋ መቆጣጠሪያ፣ የፈቃደ ነፍስ ማበልጸጊያ መሣርያ ነው፤ እነሙሴ፣ እነኤልያስ እና እነዳንኤል ከእግዚአብሔር ጋራ በቀጥታ ይገናኙ የነበረው ራሳቸውን በጾም ለእግዚአብሔር በማስገዛት ነው፡፡

ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ዓርባ መዓልትና ዓርባ ሌሊት ጾሞ፣ በሰይጣን የቀረበለትን ፈተና አሸንፎ፣ የጾምን ድል አድራጊነት በተግባርና በትምህርት አሳይቶናል፤ (ማቴ. ፬÷፩ -፲፩)
ቅዱሳን ሐዋርያትም እግዚአብሔር ሥራቸውን እንዲያቃናላቸው፣ ኃይለ መዊዕ (የአሸናፊነት ኃይል) እንዲሰጣቸው በየጊዜው ይጸልዩ ነበር፤ (ግብ. ሐዋ. ፲÷፳፫)
ሐዋርያዊት፣ ጥንታዊትና ህልውት በኵሉ የኾነች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ከነቢያት፣ ከጌታችንና ከሐዋርያት በተማረችው ትምህርትና በተቀበለችው ትውፊት መሠረት ከእግዚአብሔር ጋራ ለመገናኘት፣ ኃይለ አጋንንትን ድል ለማድረግ፣ ከእግዚአብሔር በረከትንና ረድኤትን ለማግኘት ጾምን ትጾማለች፡፡
ሰው በተፈጥሮው እርስ በርስ የሚጋጩ ኹለት ፍላጎቶች በውስጡ እንዳሉ ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል፤ እነዚኽ ፍላጎቶች ሥጋዊና መንፈሳዊ ተብለው የሚታወቁ ሲኾን፣ የሥጋ ፍላጎት ለነፍስ ፍላጎት፣ የነፍስ ፍላጎትም ለሥጋ ፍላጎት ተቃራኒ እንደኾነ በቅዱሳት መጻሕፍት ተብራርቶና ተገልጾ ተቀምጦአል፡፡ (ገላ. ፭÷፲፮-፲፰)
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህን በተመለከተ ሲያስተምር ‹‹የሥጋ ፍላጎት ሞትን ያመጣል፤ የነፍስ ፍላጎት ግን ሰላምንና ሕይወትን ይሰጠናል፤›› ብሏል፤ (ሮሜ ፮÷፮-፰)
የጾም አስፈላጊነት የሚመነጨውም ከዚኽ መሠረታዊ ትምህርት ነው፡፡ ሥጋ ኃይልና ሙቀት ሰጪ ምግቦችን አብዝቶ በተመገበ ቁጥር ኃይል ይሰማዋል፤ በዚኽ ጊዜ ለእግዚአብሔር መታዘዝን ይዘነጋል፤ ወንድሙን ለመበደል ይፈጥናል፤ ማመዛዘን አይችልም፤ ብዙ ስሕተትንም ይፈጽማል፤ በመጨረሻም ይሞታል ማለትም ከእግዚአብሔር ጋራ አንድነትን ያጣል፤ በመንፈሳዊ እይታ ከእግዚአብሔር አንድነት መለየት እጅግ በጣም የከፋ ሞት ነው፡፡
በአንጻሩ ደግሞ ሰው ከምግብ በታቀበ ጊዜ ረጋ ብሎ ማሰብን፣ ማስተዋልን፣ ማመዛዘንን፣ ለእግዚአብሔር መታዘዝን፣ ራስን መግዛትን፣ ርኅራኄንና ቸርነትን፣ ለወንድም አዛኝነትን ገንዘብ ያደርጋል፤ በመጨረሻም ከእግዚአብሔር ጋራ አንድነቱን ያጠነክራል፤ በዚኽም የሞት አሸናፊ ኾኖ በእግዚአብሔር መንግሥት በዘላለማዊ ሕይወትና ክብር ተደስቶ ይኖራል፤
ከዚኽ አኳያ ጾም ለመንፈሳዊ ሕይወት መጎልበት፣ ራስን በመግዛት ከእግዚአብሔር ጋራ ልዩ ግንኙነትና አንድነት ለመፍጠር እጅግ አስፈላጊ ኾኖ ይገኛል፡፡
ጾማችን በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት አግኝቶ ሙሉ ዋጋ ሊያሰጠን የሚችለው ከፍቅር፣ ከምጽዋት፣ ከሰላም፣ ከጸሎትና ራስን ለእግዚአብሔር ከማስገዛት ጋራ ሲኾን ነው፡፡


የተወደዳችኹ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼ ምእመናንና ምእመናት!

በፍጹም ሓሳባችን፣ በሙሉ ኃይላችንና በፍጹም ልቡናችን ለእግዚአብሔር በምንገዛበት በዚኽ ወቅት ካለን ሀብት ከፍለን፣ በየሰፈሩ የሚገኙ ጧሪ የሌላቸው አረጋውያንን፣ አሳዳጊ የሌላቸው ሕፃናትን፣ ሠርተው ራሳቸውን መርዳት ያልቻሉ አካል ጉዳተኞችን በመርዳት ጾሙን ልንጾም ይገባል፡፡
ወርኃ ጾም በመንፈሳዊ ሕይወታችንም በሥጋዊ ኑሯችን ከምንም ጊዜ በበለጠ ግዙፍና ታላላቅ ሥራዎችን ሠርተን የምናጠናቅቅበት ጊዜ ሊኾን ይገባል፡፡
በተለይም በመንፈሳዊ ሕይወታችን ለእግዚአብሔር ያለንን ተገዥነት ለማረጋገጥ፣ በመንፈስና በጽድቅ ኾነን በየቀኑ አብዝተን የምንጾምበትና የምንሰግድበት ሊኾን ይገባል፡፡
በሥጋዊ ኑሯችንም ሥራ ከሚያስፈቱን ነገሮች ኹሉ ርቀን ቀኑን በሙሉ በሥራ ላይ የምናውልበት ሊኾን ይገባል፡፡ በመኾኑም ሕዝበ ክርስቲያኑ በአገራችን የተጀመረውን የአረንጓዴ ልማት ለማሳካት አፈርን የመገደብና መስኖን የማስፋፋት ሥራ አጠናክሮ እንዲሠራና ወርኃ ጾሙን በላቀ የሥራ ርብርብ እንዲያሳልፍ መልእክታችንን ከአደራ ጭምር እናስተላልፋለን፡፡

በመጨረሻም፡-

እግዚአብሔር አምላክ ወርኃ ጾሙን መልካም የንስሐ፣ የሰላም፣ የፍቅርና የሥራ ጊዜ አድርጎ በማስፈጸም ለጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ትንሣኤ በሰላምና በጤና እንዲያደርሰን በጾምና በጸሎት እንትጋ በማለት መልእክታችንን በድጋሚ እናስተላልፋለን፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝባችንን ይባርክ ይቀድስ አሜን!!

አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
የካቲት ፲፮ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም.

 
ዝርዝር ፅሁፍ...
<< ጀምር < ወደኋላ 1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 ወደፊት > መጨረሻ >>

ገጽ 9 ከ 22

የቤተክርስቲያን አድራሻ

የካቴድራሉ ሰበካ ጉባዔ ጽ/ቤት
ስልክ ፤ 011-1-23-35-18 / 011-1-23-35-15
አዲስ አበባ
ኢትዮጵያ
church@trinity.eotc.org.et
www.trinity.eotc.org.et

ግጻዌ

ማስታወቂያ

ለመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እድሳት የበኩልዎን አስታዋጽዖ ያድርጉ!

መርዳት የምትፈልጉ ምዕመናን ሁሉ የሚከተለውን አድራሻ መጠቀም ትችላላችሁ፡፡

አራት ኪሎ ቅርንጫፍ, ቁጥር= 0171859072600/2637 (መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እድሳት )

ብላች መላክ ትችላላችሁ፡፡