ቅ. ሥላሴ ካቴድራል

{gallery}pic-cathedral{/gallery}

ቅ. ሥላሴ ካቴድራል

{gallery}pic-cathedral{/gallery}

ቅ. ሥላሴ ካቴድራል

{gallery}pic-cathedral{/gallery}

ቅ. ሥላሴ ካቴድራል

{gallery}pic-cathedral{/gallery}

http://www.trinity.eotc-churches.org/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/46016501.jpg http://www.trinity.eotc-churches.org/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/7472451.jpg http://www.trinity.eotc-churches.org/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/395795church_4.jpg http://www.trinity.eotc-churches.org/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/357816church_5.jpg
የእስክንድርያ ፖፕ እና የመንበረ ማርቆስ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ታዎድሮስ ዳግማዊ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው

                                                   በመ/ር ዘሩ ብርሃኔ(MA)

000921

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ታዎድሮስ ዳግማዊ የአሌክሳንድሪያ ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ማርቆስ መንበረ ፓትርያርክ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በመስቀል ደመራ በዓል ላይ እንዲገኙ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በተደረገላቸው ግብዣ መሠረት ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል።
በዚሁም መሠረት ቅዱስነታቸው መስከረም 14 ቀን 2008 ዓ.ም. ከሌሊቱ 9:00 ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በሚደርሱበት ጊዜ  በሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት  ደማቅ አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆነ በነጋታው ቅዳሜ መስከረም 15 ቀን 2008ዓ.ም በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፤ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጰሳት ፣  የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ኃላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማት እና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ መዘምራንና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች፣ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተገኙበት፣ ‹‹የእንኳን ደኅና መጡ›› ፕሮግራም ተከናውኗል፡፡ ቅዱስነታቸውም በበአሉ ላይ  ለተገኙ ህዝበ ምእመናን ቡራኬ ሰጥተዋል፡፡
ቅዱስነታቸው  ስለ ሁለቱም አብያተ ክርስቲያናት ታሪካዊ ግንኙነት በሰፊው ከገለፁ በኋላ ኢትዮጵያ ለዕድገቷ የምታከናውናቸውን ተግባራት የግብፅ ቤተክርስቲያን እንደምትደግፍ ተነግረዋል። "አንድ ከሚያደርጉንና ከሚያስተሳስሩን ጉዳዮች ዋናው ነገር የዓባይ ወንዝ ነው" ያሉት አቡነ ታዎድሮስ "የአገራቱ መሪዎችም ምንም ዓይነት ልዩነትና ፀብ እንደማይፈጥሩ እርግጠኞች ነን" ብለዋል። "የዓባይ ወንዝ እግዚአብሔር በነፃ የሰጠን ስጦታ ነው፣ ሁሉም የሰው ልጆች ከፀሐይና ከነፋስ በነፃ እንደሚጠቀሙ ሁሉ ከዚህም ወንዝ በነፃ ይጠቀማሉ ይህንንም ስጦታ በነፃ እየተጠቀምን በፀጋ እንኖራለን" ሲሉ ነው የተናገሩት።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ አቡነ ማትያስ በበኩላቸው አገራቱ ባህልን፣ ቋንቋን፣ሥነ ጽሑፍን፣ ንግድን፣ መንፈሳዊና ማሕበራዊ ጉዳዩችን ያካተተ የቆየ ግንኙነት እንዳላቸው ጠቅሰዋል።"ከዚህም ባለፈ የአባይ ወንዝን በጋራ የምንጠጣ ታሪካዊያን ሕዝቦች ነን" ሲሉ ተናግረዋል።
ወንዙን በአግባቡና በፍትኃዊነት ከተጠቀምንበት ለሌሎች አገራት ጭምር የሚበቃ ማለቂያ የሌለው የአምላክ በረከት መሆኑን ገልፀዋል።ይህን ወንዝ በሠላማዊ መንገድ በመጠቀም የሁለቱ አገራት መንፈሳዊና ማኅበራዊ ግንኙነቶች ለዓለም ምሣሌ በሚሆን መልኩ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው አባታዊ ምክራቸውን አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስና የግብፅ ኮፒቲክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያናት መንፈሳዊ ግንኙት ከ1 ሺህ 600 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ መሆኑን የታሪክ ድርሳት ያስረዳሉ።

 
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የ2008 ዓ.ም የዘመን መለወጫ መልእክት አስተላለፉ

0908

ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በእንተ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወሰምንቱ ዓመተ ምሕረት
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
-በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣
-ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤
-የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤
-በሕመም ምክንያት በየፀበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤
-እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤
የዘመናት ፈጣሪ የሆነው አምላካችን እግዚአብሔር ያለፈውን ዓመት በሰላም አስፈጽሞ እንኳን ለአዲሱ የሁለት ሺሕ ስምንት ዓመተ ምሕረት ዘመነ ዮሐንስ በሰላም አደረሰችሁ!!
‹‹ወኀሊ ዓመተ ለትውልደ ትውልድ፤ የብዙ ትውልድን ዓመታት አስብ›› (ዘዳ. 32፡7)፡፡
የሁሉም አስገኝና ፈጣሪ የሆነው እግዚአብሔር አምላካችን ከፈጠራቸው ፍጥረታት መካከል አንድ ስንኳ ጥቅም የለሽ የሆነ ፍጥረት አይገኝም፡፡
ፍጥረታት ሁሉ በእርሱ ዘንድ ውብና የየራሳቸው ዓላማና ተግባር ያላቸው ናቸው (ዘፍ.1፡25)
እግዚአብሔር የፈጠራቸው ፍጥረታት በፍጡር ዓቅም ሙሉ በሙሉ ተቆጥረው የሚዘለቁ አይደሉም፤ ከጥቂቶቹ በስተቀር ሁሉንም በዓይነ ፍጡራን ማየት ስለማይቻል ቅዱስ መጽሐፍ ፍጡራንን ጠቅለል አድርጎ በአጭር ቃል ሲገልጽ ‹‹በሰማይና በምድር ያሉት፣ የሚታዩትና የማይታዩት›› ይላቸዋል፤ (ቈላ. 1፡15)
በምድር ላይ እያሉ ከማይታዩት መካከል አንዱ ዘመን ወይም ጊዜ ነው፤ ጊዜ በድርጊት ከሚታወቅ በቀር በዓይን የሚታይ ግዙፍ አካል ወይም ልዩ ቀለም ያለው ፍጡር አይደለም፡፡ይሁን እንጂ ባለመታየቱ ብቻ የለም ብሎ መደምደም ወይም መናገር አይቻልም፤ ምክንያቱም ከድቁቅ ስፍረ ጊዜ አንሥቶ ሰዓታትን በቀናት፣ ቀናትን በሳምንታት፣ ሳምንታትን በወራት፣ ወራትን በዓመታት ከዚያም በልዩ ልዩ አዕዋዳት እየጠቀለለ ሲያሽከረክር በተግባር እናያለንና ነው፡፡ዘመን የድርጊት መሣሪያ ስለሆነ በአንድ ወቅት በተፈጸመ መልካም ወይም መጥፎ ነገር ይገለጻል፤ ከዚህም የተነሣ ዘመኑ መልካም ነው ወይም መጥፎ ነው ሲባል እንሰማለን ፡፡
ይሁንና የእኛ መሠረታዊ ጉዳይ ሊሆን የሚገባው የዘመን መታየትና አለመታየት ሳይሆን ለፍጡራን ከሚሰጠው ጥቅም አኳያ ግንዛቤ ወስደን ተጠቃሚ ለመሆን መንቀሳቀሱ ላይ ነው ፡፡
ዘመን ከዓለም መፈጠር በፊት ያልነበረ ከዓለም ጋር አብሮ የተፈጠረ፣ በሰማይ የሌለና ለምድራውያን ፍጡራን ብቻ አገልግሎት ሊሰጥ የተፈጠረ ነው፤ (ዘፍ.1፡14) ፡፡
የዘመን ሀብት ባይኖር ሰው ምድራዊ ሕይወቱን በትክክል መምራት አይችልም ነበር፡፡በመሆኑም ምድራውያን ፍጥረታት በአጠቃላይ፣ በተለይም ደግሞ የሰው ልጅ ሥርዓት ባለውና ቅደም ተከተሉን ጠብቆ በዕቅድ ሥራውን በማከናወን ሕይወቱን በትክክል መምራት ይችል ዘንድ ሀብተ ዘመን ያስፈልገዋል ፡፡ዘመን ለተግባር ከሚያበረክተው አገልግሎት በተጨማሪ በትምህርት ሰጪነቱ እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ ያለፈውን ዘመን እንድናስታውስ እንጂ እንዳንረሳ የልጅ ልጅ ዘመናትን አስብ ብሎ እግዚአብሔር ይነግረናል፡፡ምክንያቱም ለወደፊቱ የተሻለ ሥራ መሥራት የምንችለው ካለፈው ዘመን ትምህርት ቀስመን፣ ልምድና ተሞክሮ ወስደን ስለሆነ ነው፤ ሥራን ከዘመን ለይቶ ወይም ነጥሎ ማስቀመጥ በፍጹም አይቻልምና ፡፡
ስለሆነም ዘመን ለአጠቃላዩ ሥራችን ተቀዳሚ መሣሪያ ሆኖ እንዲያገለግለን እግዚአብሔር የሰጠን ሀብት ነውና ጊዜን በከንቱ ሳናባክን በምልአት ልንጠቀምበት ይገባል ፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!!
ሀገራችን ኢትዮጵያ ሁሉንም የተፈጥሮ ሀብት ተሟልቶ የተሰጣት፣ ድንቅና ውብ ሀገር ናት፤
ምድራዊት ገነት በሆነች በዚች ሀገር ተቀምጠን ስለድህነት ማውራት ከእንግዲህ ወዲህ እንዲያከትም ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድነት መረባረብ አለበት፤
ልማታችንን በአስተማማኝ ደረጃ ዘላቂ ለማድረግ የድህነታችን ምሥጢር የት እንዳለ በውል ማወቁ ይጠቅማል ፡፡እንደ እውነቱ ከሆነ የድህነታችን ምሥጢር ተደብቆ ያለው የሥራ ባህልን አዳብሮ፣ የጊዜን ጥቅም አውቆና አንዲት ደቂቃ ስንኳ ሳያባክን በሀገሩ ውስጥ ሠርቶ ለመለወጥ ያለን ተነሣሽነት አናሳ መሆኑ ላይ ነው፡፡ በተለይም ወጣቱ ትውልድ ይህንን ተገንዝቦ መሠረታዊ የአስተሳሰብና በጊዜ ሠርቶ የመለወጥ ባህል ሊያጎለብት ይገባል፤ ይህንን ክፍተት በውል ስናውቅና በሥራ ስንታገለው ድህነትን ከሥር መሠረቱ ነቅለን መጣል እንችላል ፡፡
ዛሬ አደጉ በለፀጉ ተብሎ የሚነገርላቸው ሀብታም ሀገሮች አብዛኛዎቹ እንደ ኢትዮጵያ ያለ ለእርሻና ለልዩ ልዩ አዝርእት የተመቸ ለም መሬት፤ ለእንስሳ ርባታና ለሰው ኑሮ የተመቸ አየርና  ንጹሕ ውሀ፣ በልዩ ልዩ ማዕድን የተሞላ ነገር ግን ገና ያልተፈተሸ ድንግል መሬት ኖሮአቸው ሳይሆን፣ ያላቸውን ውሱን ሀብት በበለፀገ የሥራ ባህል ማለትም ሥራን ሳያማርጡ፣ ጊዜን በከንቱ ሳያባክኑ ያለ ዕረፍት ሌት ተቀን በመሥራታቸው ያገኙት ጸጋ እንደሆነ ማስተዋል አለብን ፡፡
በመሆኑም ኅብረተ ሰባችን በአጠቃላይ በተለይም ወጣቱ ትውልድ አዲሱን ዘመን ሲቀበል አዲሱን ዓመት ከሀገራችን የሕዳሴ መርሐ ግብር ጋር በማቀናጀትና ጠንክሮ በመሥራት ግዙፍ የሆነ የልማትና የዕድገት ስኬት ለማረጋገጥ ከዳር እስከ ዳር ተባብሮ እንዲንቀሳቀስ አባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን መልካም አዲስ ዓመት ያድርግልን፡፡
እግዚአብሔር ይባርካችሁ ይቀድሳችሁ አሜን
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
መስከረም 1 ቀን 2008 ዓ.ም.
አዲስ አበባ፣
ኢትዮጵያ

 
የሐምሌ ሥላሴ በዓለ ንግሥ በመንበረ ጸባዖት ቅድሥት ሥላሴ ካቴድራል ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ተከብሮ ዋለ!!

2648

በየዓመቱ ሐምሌ 7 ቀን የሚከበረው የአጋዕዝተ ዓለም ሥላሴ መለኮታዊ በዓለ ንግሥ በዘንድሮው ዓመት 2007 ዓ.ም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትና በርካታ ምዕመናን በተገኙበት በታላቅ ድምቀት የተከበረ ሲሆን ሥርዓተ ቅዳሴው በብፁዕ አቡነ ሄኖክ የምሥራቅ ወለጋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተመርቶአል፡፡
በሥርዓተ ቅዳሴው አጋማሽ ላይ “የእግዚአብሔር ቸርነት ምድርን ሞላች ፣ በእግዚአብሔር ቃል ሰማዮች ፅኑ ፣ ሠራዊታቸው ሁሉ በአፉ እስትንፋስ” መዝ 33፤6 የሚለው የዳዊት መዝሙር በዜማ ተሰምቶአል፡፡ በመቀጠልም “ዮሐ 8፤51 ላይ እውነት እውነት እላችኋለሁ ቃሌን የሚጠበቅ ቢኖር ለዘለዓለም ሞትን አያይም የሚለው የወንጌል ቃል ተነቧል፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ የበዓሉ መሠረታዊ የት መጣ በኦሪት ዘፍጥረት ምዕ 20 እና 22 ላይ የተመሠረተው የአባታችን የአብርሃም ታሪክ የተፈጸመበት ጥንተ ታሪክ ነው፡፡ አብርሃም የጣኦት አምልኮ ከተስፋፋበት ከካራን በመውጣት ወደ ተቀደሰችው ምድረ ርስት ወደ ከነአን የገባበት ታሪክ ሲሆን ከካራን ከወጣ በኋላ እግዚአብሔር አብርሃምን ለመፈተን እና የእምነቱን ፅናት ለማረጋገጥ አብርሃምን ልጅህ ይስሐቅን ሰዋልኝ ባለው ጊዜ አብርሃም ሳያመነታ ፣ ልጁን ይስሐቅን አስከትሎ ፣ እንጨት፣ ቢላዋና እሳት ይዞ ወደ መሰዊያ ቦታ ወደ ተራራ ወጣ፡፡
አብርሃም ልጁ ይስሐቅን ለእግዚአብሔር መስዋዕት አድርጎ ለማቅረብ ዝግጁ ቢሆንም እግዚአብሔር ግን ለይስሐቅ ተለዋጭ የሆነ ቀንዶቹ ብዕፀ ሳቤቅ የታሠሩ ነጭ በግ በማቅረቡ ከሰማይ የተላከው ነጭ በግ የይስሐቅ ተለዋጭ በመሆን የተሰዋ መሆኑን ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በድርሰቱ ሲአብራራ “አብርሃም ወሰዶ ለይስሐቅ ወልዱ ከመይሱኦ አውረደ ሎቱ ቤዛሁ በግአ” በማለት አብራርቶአል፡፡ ከሰማይ የወረደው የይስሐቅ ተለዋጭ የሆነው ያ በግ የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ መሆኑን የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ይገልፃሉ፡፡ 
በዚሁ እለት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ታለቁንና መለኮታዊ የሆነውን የአጋዕዝተ ዓለም ሥላሴን በዓል አስመልክተው ያስተላለፉትን ትምህርትና ቃለ በርከት እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
ዘአቀበ ቃልየ ኢይጥእሞ ለሞት ዮሐ 8፤5
በዚህ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ የተሰበሰብን የሥላሴ ፍጡሮች ነን፡፡ ሥላሴ ሰማዩን፣ ምድሩን፣ ሰውን እና እንስሳውን የፈጠሩ ናቸው፡፡ ጸሎታችንን ተቀብለው የለመናቸውን ይሰጡናል፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቃሌን የጠበቀ ሞትን አያይም ብሏል፡፡ አይሁድ ግን አባታችን አብርሃም ሞቷል አንተ ከማን ትበልጣለህ አሉት፡፡ አይሁድ ሳይገባቸው ጌታን ነቀፉት ፤ ሰው የጽድቅን ሥራ ከሠራ ዘለዓለማዊ ሕይወት ያገኛል፡፡ ስለዚህ ክርስቲያን የእግዚአብሔር ስጦታ ይጠብቀዋል፡፡ ሁሉም መንገደኛ ነው ፤ በዚህ ዓለም ላይ ሆነን ድሆችን በመርዳት የታመሙትን በመጠየቅ የተጨነቁትን በማጽናናት መልካም ሥራ መሥራት አለብን፡፡
ሥላሴ በመካከላችን አሉ ፤ ቃሉን ጠብቀን ከኖርን የመንግሥተ ሰማያት ዜጎች እንሆናለን፡፡ ቃሉን የጠበቀ ሞተ ነፍስን አይቀምስም ሥለሴ በአብርሃም ቤት ተስተናገዱ በሚለው መሠረትነት ነው በዓላችንን ያከበርነው ፤ ሥላሴ በረከታቸውን ያሳድሩብን በማለት ቅዱስነታቸው ሰፋ ያለ መልእክት ካስተላለፉ በኋላ የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል፡፡

 
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የ2007 ዓ.ም. የትንሣኤ በዓልን አስመልክተው መልእክት አስተላለፉ

0908

ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በእንተ ትንሣኤሁ ለእግዚእነ ወአምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ሎቱ ስብሐት፡፡
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ፡፡
- በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣
- ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤
- የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤
- በሕመም ምክንያት በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤
- እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤
በሞትና በመቃብር ላይ ሥልጣን ያለው ኃያሉና አሸናፊው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም አደረሳችሁ ፡፡
‹‹ወበከመ በእንተ አዳም ኵልነ ንመውት ከማሁ በክርስቶስ ኵልነ ነሐዩ፤ ሁላችን በአዳም እንደምንሞት እንደዚሁም ሁላችን በክርስቶስ ሕያዋን እንሆናለን›› (1ቆሮ. 15÷22)፡፡
እዚህ ላይ በተገለፀው ቃለ እግዚአብሔር መሠረት የሰዎች መጻኢና የመጨረሻ ዕድል ከሁለት አዳማዊ ውርስ ጋር የተያያዘ ሆኖ ይገኛል ፡፡
በቅዱስ መጽሐፍ በግልጽ እንደተጻፈው ሰው ሁሉ ከቀዳማዊ አዳም በሥጋ ተወልዶአል፤ የእርሱ የሆነውንም ሁሉ ወርሶአል፤
ይህም ማለት በሥጋው በኩል የግብረ ኃጢአት ዝንባሌን፣ ሞተ ሥጋን፣ ወሪደ መቃብርን፣ በመቃብር ውስጥ መበስበስንና መፍረስን ሲወርስ በነፍሱ በኩል ደግሞ ከእግዚአብሔር መለየትን፣ በኃጢአት ተሸንፎ የዲያብሎስ ሎሌ መሆንን፣ በኃጢአቱ ምክንያት ለኵነኔ ሲኦል ተጋላጭ መሆንን እና የመሳሰሉትን ሁሉ ወርሶአል ማለት ነው፡፡
ጠቅለል አድርገን ስናየው ቀዳማዊ አዳም በሥጋና በነፍስ ከባድ ውድቀትን ለልጆቹ አውርሶአል ማለት ነው ፡፡
ከቀዳማዊ አዳም የውድቀት ዘመን ጀምሮ እስከ ስቅለተ ክርስቶስ በነበረው ረጅም ዘመን የሰው ዘር በአጠቃላይ ከቀዳማዊ አዳም ባገኘው ውርስ ምክንያት በሥጋው ርደተ መቃብርን፣ በነፍሱ ርደተ ሲኦልን ተፈርዶበት በድርብ መከራ ሲማቅቅ ኖሮአል ፡፡
ያ ዘመን ከመከራው ብዛት የተነሣ ዓመተ ፍዳ፣ ዓመተ ኵነኔ ፣ ዓመተ መርገም ተብሎ ተሰይሞአል ፡፡
ይሁን እንጂ ለምሕረቱና ለይቅርታው ወሰን የሌለው እግዚአብሔር አምላክ የሰውን ውድቀት በትንሣኤ ለመቀልበስ ሲል የባህርይ ልጁ የሆነ እግዚአብሔር ወልድን ወደዚህ ዓለም ላከ፡፡
እርሱም የኛን ሥጋ ተዋሕዶ ሰው ሆነ፤ በመካከላችን ተገኝቶም ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከመቃብር ወደ ትንሣኤ የሚወስደውን መንገድ በቅዱስ ወንጌሉ አስተማረን ፤ (ዮሐ.5÷24)
የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ በመለኮቱ የአብ ልጅ ቢሆንም በሥጋው የሰው ልጅ ነውና ዳግማዊ አዳም ተብሎ ይጠራል (1ቆሮ15÷45 – 48)፡፡
በመሆኑም ዳግማዊ አዳም የተባለው ጌታችን፣ አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በበኩሉ ቀዳማዊ አዳም ለልጆቹ ላወረሰው ውርስ ተቃራኒ የሆነውን ለሰው ዘር ሁሉ አውርሶአል፤ ይኸውም፡-
- በኃጢአት ዝንባሌ ፈንታ ጽድቀ መንፈስን፣
- በሞት ፈንታ ዘላለማዊ ሕይወትን፣
- በርደተ መቃብር ፈንታ ትንሣኤን፤
- በርደተ ሲኦል ፈንታ ዕርገትን፣
- በመለያየት ፈንታ ከእግዚአብሔር ጋር በአንድነት መኖርንና የመሳሰሉትን ለልጆቹ አውርሶአል፡፡
ይህ ሁሉ በክርስቶስ ቤዛነት ምክንያት ለሰው ልጅ በመሰጠቱ ከክርስቶስ ልደት ወዲህ ያለው ዘመን ዓመተ ሥጋዌ፣ መዋዕለ ንሥሐ፣ ዓመተ ምሕረት ተብሎ ይጠራል፡፡
ይሁንና ሰው ሁሉ ከቀዳማዊ አዳም በሥጋ ዘር በመወለዱ የእርሱ የሆነውን ሁሉ እንደወረሰ፣ አሁንም በተመሳሳይ ሁኔታ የዳግማዊ አዳም የሆነውን ሁሉ ለመውረስ ከዳግማዊ አዳም በመንፈስ መወለድ የግድ ያስፈልገዋል፡፡
ሰው በእምነት ተፀንሶ በጥምቀት ከመንፈስ ቅዱስ ሲወለድ የዳግማዊ አዳም ልጅ ይሆንና የእርሱ የሆነውን ሁሉ ይወርሳል፤ ከዚህ ዳግም ልደት በመንፈስ የተወለዱ ሰዎች ሁሉ የቀዳማዊ አዳም ውርስ አይነካቸውም (ሮሜ.8÷1 )፡፡
የዳግማዊ አዳም ውርስ በዳግም ምጽአተ ክርስቶስ እውን ለማድረግ ቀጠሮ ተይዞለታል፤ ያን ጊዜ በመቃብር ያሉ ሙታን ሁሉ በቅፅበት ሲነሡና በሕይወት ያሉትም በአንድ ጊዜ በቅፅበት ሲለወጡ የዳግማዊ አዳም ውርስ በግልጽ ይታያል ፡፡
በዚህ ጊዜ የሚሞተውና የሚበሰብሰው አካላችን የማይሞተውንና የማይበሰብሰውን ሲጎናፀፍ ሞትና መቃብር ይሸነፋሉ፤ ህልውናቸውም ያከትማል፡፡ /1ቆሮ. 15÷52-57)
በዚያን ጊዜ ከቀዳማዊ አዳም በመጣ የኃጢአት ውርስ ምክንያት የሞቱ ሁሉ ከዳግማዊ አዳም በተገኘ የጽድቅ ውርስ ምክንያት ሕያዋን ሆነው ይነሣሉ /1ቆሮ.15÷49)
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት፤
ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሙስና መቃብርን አጥፍቶና ሞትን ድል አድርጎ የተነሣበትን በዓለ ፋሲካ ዛሬ በታላቅ ድምቀትና በደስታ ማክበራችን ‹‹ሞቴንና ትንሣኤዬን አስቡ›› (1ቆሮ.11÷26) ያለውን ቃሉን ከመፈጸም ባሻገር የኛንም ትንሣኤ በእርሱ ትንሣኤ እያየን በሃይማኖትና በማይናወጽ ተስፋ ፀንተን እንድንኖር ለማድረግ ነው፡፡
በእርግጥም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤዛነቱ ካቀዳጀን ጸጋ አንዱና ዋነኛው እኛን ለትንሣኤና ለዘላለማዊ ሕይወት ማብቃቱ ነው፡፡
ከጌታችን ትንሣኤ የምንገነዘበው ዓቢይ ነገር እርሱ በመቃብር ውስጥ ሙስና መቃብር ማለትም መበስበስና መፍረስ ሳይነካው ሞትን ድል አድርጎ በመነሣት ወደሰማያዊ ክብሩ እንዳረገ፣ እኛም ከእርሱ በወረስነው የጽድቅ ውርስ መሠረት እንደእርሱ ከመቃብር ተነሥተንና የዘላለምን ሕይወት ተቀዳጅተን ወደሰማያዊ መንግሥቱ የምናርግ መሆናችንን ነው፡፡
የክርስቶስ ትንሣኤ የትንሣኤያችን ማሳያ መስተዋትና የዘላለማዊው ሕይወታችን ማረጋገጫ ነውና (1ተሰ.4÷13 – 18)፡፡
ይሁን እንጂ የትንሣኤያችን ጉዞ የሚጀምረው ዛሬ በሕይወተ ሥጋ እያለን መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡
ገበሬ በመኸር ወራት ጥሩ ምርትን ለማፈስ ልፋቱን በግንቦትና በሰኔ እንደሚጀምር፣ ያን ካላደረገ ደግሞ የሚያገኘው ምርት እንደማይኖር ሁሉ፣ እኛም የትንሣኤያችን ሃይማኖታዊና ሥነ ምግባራዊ ጉዞ ዛሬ በዚህ ዓለም ሳለን ካልጀመርነው በዳግም ምጽአት የምናገኘው ነገር አይኖርም (ማቴ 25÷ 1 – 13)፡፡
ሁላችንም እንደምንገነዘበው አምላካችን እግዚአብሔር ሠርቶ የሚያሠራ አምላክ እንጂ መክሊቱን ቀብሮ በስንፍና የሚኖረውን የሚወድ አምላክ አይደለም፤(ማቴ.25÷24 – 30)
አምላካችን ከባህርይ አምላክነት በስተቀር ሁሉን በሁሉ የሚያሳትፍ አምላክ እንደሆነ ምን ጊዜም አንርሳ፤ ቅዱስ ተብሎ ቅዱሳን እንድንባል፣ ጻድቅ ተብሎ ጻድቃን እንድንባል፣ ክቡር ሆኖ ክቡራን እንድንሆን፣ ሕያው ሆኖ ሕያዋን እንድንሆን ፈቅዶልናል (1ጴጥ. 1÷16)፡፡
በመሆኑም እርሱ የመልካም ሥራ ሁሉ ባለቤት እንደሆነ እኛም የመልካም ሥራ ባለቤቶች በመሆን ትንሣኤያችንን ከዚህ እንድንጀምር ተሳትፎውን ማለትም እርሱን መምሰልን ከእኛ ይፈልጋል፡፡ /ማቴ. 5÷48)
ዛሬ ዓለማችን በፀጥታ እጦት እየታመሰች የምትገኘው ከሥነ ምግባር ጉድለት የተነሣ እንደሆነ ሁሉም ሊያውቀውና ሊገነዘበው ይገባል ፡፡
በልዩ ልዩ የዓለማችን ሀገራት ውስጥ የሚገኙ የትምህርት ተቅዋማት የሥነ ምግባር ትምህርትን እያስተማሩ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ዓለማችን በመልካም ሥነ ምግባር ከመበልፀግ ይልቅ በዘቀጠና ለአእምሮ በሚዘገንን ነውረ ኃጢአት ክፉኛ እየተናጠች ትገኛለች ፡፡
ይህ ሁሉ የሥነ ምግባር ውድቀት ሊመጣ የቻለው በየትምህርት ቤቱ የሚሰጠው የሥነ ምግባር ትምህርት በፈሪሀ እግዚአብሔር ያልተቃኘ ከመሆኑ የተነሣ እንደሆነ ሊሠመርበት ይገባል (መዝ. 110÷10፤ 1ቆሮ 1÷20 – 21)፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!
ኢትዮጵያ ሀገራችን በእግዚአብሔር ፊት ልዩ ተቀባይነት ያላት ሀገር እንደሆነች ቅዱስ መጽሐፍ ሊመሰክርላት የቻለው በተቀደሰው ባህሏና በመልካም ሥነ ምግባሯ፣ በጸናው ሃይማኖቷና በእውነተኛው ትውፊቷ እንጂ በሌላ በምንም እንዳልሆነ በአጽንኦት መገንዘብ ያሻል፡፡ (መዝ. 71፡9፤ 67፡31)
በሀገራችን ከምናስታውሰው ነባሩና ሃይማኖታዊ ባህላችን አንዱ ለብቻ መመገብ እንደነውር የሚወሰድ መሆኑን ነው፡፡ ይህ መልካም ሥነ ምግባራችንና ቅዱስ ባህላችን ዛሬም ተጠብቆ እንዲቀጥል ማድረግ የሁላችንም ኃላፊነት ነው ፡፡
የትንሣኤያችንን ጉዞ ዛሬ እንጀምር ስንል የተራበውን ማጉረስ፣ የተጠማውን ማጠጣት፣ የታረዘውን ማልበስ፣ ያዘነውን ማጽናናት፣ የታመመውን መጠየቅና መርዳት፣ ስደተኛውን ማስተናገድ፣ የታሠረውን መጠየቅ፣ የሥራ ጊዜን በአልባሌ ቦታ አለማጥፋት፣ ለሰላም፣ ለሀገር ልማትና ለዕድገት በአንድነት መሰለፍ፣ ሁሉንም ነገር በፍቅርና በስምምነት ብቻ መፍታት የመሳሰሉትን ሁሉ የሕይወታችን መርሆዎች አድርገን በተግባር እናውላቸው ማለታችን ነው፤ ይህንን የምናደርግ ከሆነ እውነትም የትንሣኤን ጉዞ በትክክል ጀምረናል ማለት ነው ፡፡
በመጨረሻም
ሁላችሁም ኢትዮጵያውያን ልጆቻችን በተቀደሰው እምነት ጸንታችሁ፣ ፈሪሀ እግዚአብሔርን መሠረት ያደረገ ሥነ ምግባር አንግባችሁ፣ የሀገራችንን ሰላም በጽኑ እንድትጠብቁ፣ ልማቷንና ዕድገቷን እንድታፋጥኑ፣ አንድነታችሁንና እኩልነታችሁን አጥብቃችሁ እንድትይዙ፣ በዓለ ፋሲካውንም የተራቡትን በመመገብ፣ የታረዙትን በማልበስና የተጠሙትን በማጠጣት፣ በሰላምና በፍቅር እንድታከብሩ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን ፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር! አሜን!
 እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝባችንን ይባርክ አሜን
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ሚያዝያ 4 ቀን 2007 ዓ.ም.
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

 
የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖ 2ኛ ዓመት በዓለ ሲመት ተከበረ

0019

የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት 2ኛ ዓመት የፕትርክና በዓለ ሲመት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የካቲት 24 ቀን 2007 ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ የሃይማኖት መሪዎች፤ የመንግሥት ባለ ሥልጣናት፤ አምባሳደሮች፤ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያ ኃላፊዎች፤ የድርጅት ኃላፊዎች፤ የኮሌጅ ኃላፊዎች፤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፤ ሠራተኞች፤ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ካህናት፤ ምዕመናንና ምዕመናት በተገኙበት በታላቅ መንፈሳዊ ድምቀት ተከብሯል፡፡
ቅዱስነታቸው በበዓሉ ላይ በሰጡት ቃለ ምእዳን “የእግዚአብሔር መንግሥት ማእከል የሆነችው ቤተ ክርስቲያን ጌታችን በሐዋርያት እንድትጠበቅ አድርጓል፡፡ ሐዋርያትም በበኩላቸው በተኳቸው ጳጳሳት እና ቀሳውስት ጠባቂነት ቤተ ክርስቲያን እንድትመራና እንድትጠበቅ አድርጓል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ሐዋርያዊት፤ አንዲትና ቅድስት እንደመሆኗ መጠን ከመጀመሪያው አንስቶ መንፈሳዊውን ጥበቃ በጳጳሳትና በቀሳውስት ስታከናውን ኖራለች፡፡ አሁንም እያከናወነች ነው፤ ወደፊትም በዚሁ ትቀጥላለች” ብለዋል፡፡
ቅዱስነታቸው አያይዘውም ጳጳሳትና ቀሳውስት የተሰጣቸውን የጠባቂነት ሚና አስመልክቶም “ይሁንና በዘመናችን እየተነሳ ያለው መሠረታዊ ጥያቄ የእግዚአብሔር መንግሥት ተጠሪ የሆኑት ጠባቂዎች ሓላፊነታቸውን በሚፈለገው ሁኔታ እየተወጡ ነው ወይ? የሚለው ጥያቄ በአሁኑ ጊዜ ዓለም አቀፋዊና የወቅቱ ጥያቄ ሆኖ ይገኛል፡፡ የእግዚአብሔር መንጋ የሆኑት ክርስቲያኖችን በባሕር ማእበል ሞገድ እንደሚናጥ መርከብ በጥርጣሬ እየተናጡ አጉል መንገድ ላይ እንዲቀሩ እያደረገ ነው፡፡ ከመንጋው ተነጥሎ እንደሚቅበዘበዝ በግ ባለማመን ማእበል እያንጓለሉት ነው፡፡ በጠባቂነት የተሾምን ሁሉ ከተጠያቂነት ለመዳን በዛሬው እለት የበዓለ ሲመተ ክህነትን ለማክበርና ማሰብ በተሰባሰብንበት ቀን የመንጋ ጥበቃ ሥራችን የት ላይ እንዳለ ማሰላሰል አለብን፡፡ መንጋው እየበዛ ነው ወይስ እየቀነሰ፤ ጤናማ ነው ወይስ በሽተኛ? የሚለውን ጥያቄ አንስተን ተጨባጭ መልስ ልንሰጥ ይገባል” በማለት ተናግረዋል፡፡
ከተወቃሽነት ለመዳን መደረግ ስለሚገባው አገልግሎት ሲገልጹም “የተመረጥንበት የጥበቃ ሓላፊነት በትክክል ካልሰራንበት በመንጋውም፤ በታሪክም፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ በእግዚአብሔር ፊት ወቀሳ እንደማይቀርልን ተገንዝበን ከተጠያቂነትና ከተወቃሽነት ለመዳን የጥበቃ ሥራችንን በርትተን መሥራት ይገባናል፡፡ የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ ተብለናልና” ብለዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፤ የወላይታ ኮንታ ደውሮ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በበኩላቸው 56ኛውን በዓለ ሲመተ ፕትርክና እና 2ኛውን የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በዓለ ሲመተ ፕትርክናን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልእክት “እግዚአብሔር ለቅዱሳን ያለው ፍቅር በርቀት የሚመዘንና የሚለካ አይደለም፡፡ እነሱ በአጠገቡ ሆነው የእሱን ሥራዎች እንዲሠሩ ፈቅዶላቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በምድር ላይ መጋቢዎች፤ እንዲሁም አስታራቂዎች አድርጓቸዋል፡፡ “ለአባቶቻችን ያዘዘውን ለሚመጣው ትውልድ ለልጆቻቸው ያስታውቋቸውም ዘንድ አልሰወሩም” እንዲል ቅዱስ ዳዊት ዛሬ በዚህ ዐውደ ምሕረት ላይ እንደምንመለከተው ቅዱስነትዎ ከአባቶችዎ የተረከቡትን ሓላፊነት በታማኝነት ለመጠበቅ ቃል የገቡበትን እለት ለማስታወስ ነው” ብለዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የስብከት ወንጌል መምሪያ የበላይ ጠባቂና የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ  በቅዱስ ፓትርያሪኩ ትምህርት እንዲሰጡ የተጋበዙ ሲሆን ቅኔውንና ትምህርቱን አዋህደውና አዋዝተው ሰማዕያኑን እጅግ በአስደነቀ መልኩ አቅርበዋል፡፡

በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያሪክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፤ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም፤ ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ሰጥተው የበዓሉ ፍፃሜ ሁኗል።

 
ዝርዝር ፅሁፍ...
<< ጀምር < ወደኋላ 1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 ወደፊት > መጨረሻ >>

ገጽ 7 ከ 22

የቤተክርስቲያን አድራሻ

የካቴድራሉ ሰበካ ጉባዔ ጽ/ቤት
ስልክ ፤ 011-1-23-35-18 / 011-1-23-35-15
አዲስ አበባ
ኢትዮጵያ
church@trinity.eotc.org.et
www.trinity.eotc.org.et

ግጻዌ

ማስታወቂያ

ለመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እድሳት የበኩልዎን አስታዋጽዖ ያድርጉ!

መርዳት የምትፈልጉ ምዕመናን ሁሉ የሚከተለውን አድራሻ መጠቀም ትችላላችሁ፡፡

አራት ኪሎ ቅርንጫፍ, ቁጥር= 0171859072600/2637 (መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እድሳት )

ብላች መላክ ትችላላችሁ፡፡